
ባሕር ዳር: ሰኔ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዴት ከተማ አሥተዳደር የገነባቸውን የከተማ መሠረተ ልማቶች አስመርቋል።
የተመረቁት ልማቶች የንጹሕ መጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ የከተማ መሐል የኮሪደር ልማት፣ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ እና የወጣቶች መዝናኛ ክበብ ናቸው።
በከተማዋ ልማት እና ሰላም ላይም ከኅብረተሰቡ ጋር ውይይት ተደርጓል።
የአዴት ከተማ ነዋሪ አቶ ፈጠነ መኮነን አዴት በልማት ቀደምት የነበረች እና ኅብረተሰቡም ለልማት ቀናኢ ሕዝብ መኾኑን ገልጸዋል። በግጭት ውስጥ ኾነውም ልማቱን የሠሩ መሪዎችን አመሥግነዋል።
ሰላም ቢሰፍን አካባቢው ከዚህ የበለጠ ሊለማ እንደሚችል ጠቅሰዋል። ሰላም እንዲሰፍን መሥራት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ እማዋይ ብርሀኑ መሪዎች በሰላም እጦት ውስጥም ኾነው የሠሩትን ልማት አድንቀዋል። መሪዎች በከተማዋ ሰላም ከማስፈን በተጓዳኝ ልማቷ እንዳይቋረጥ መሥራታቸውን መመልከታቸውን ነው ያብራሩት። ይህም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
“ግጭት ውስጥ የገቡ ልጆቻችን ወደ ሰላም እንዲመጡ በየቤተሰባችን መነጋገር እና ሰላም መፍጠር አለብን” ነው ያሉት ወይዘሮ እማዋይ።
የሀገር ሽማግሌ አቶ ክንዱ ባየህም የአዴት እና አካባቢው ሕዝብ በየጊዜው በሚሠሩ ልማቶች በቅንነት እና በንቃት ተሳታፊ መኾኑን አንስተዋል።
ሕዝቡ የሰላምን ጠቀሜታ የሚገነዘብ እና ለሰላም የሚጥር ነው ብለዋል። ማኅበረሰቡ የተጀመሩትን ልማቶች ለማስቀጠል ከመሪዎች ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል። የልማት ጥያቄዎቹን በየደረጃው በመወያየት እያቀረበ መኾኑን ተናግረዋል።
በግጭት ውስጥ እንዲህ ከተሠራ ሰላም ቢኾን ኖሮ ምን ያህል የበለጠ ሊሠራ እንደሚችል መገመት ይቻላል ያሉት አቶ ክንዱ ያጋጠመን ችግርም ዘመኑን የማይመጥን ስለኾነ ወደ ሰላም መመለስ አለብን ብለዋል። ለዚህም ሁሉም በየድርሻው መሥራት እንዳለበት ገልጸዋል።
የአዴት ከተማ አሥተዳደር የሥራ እና ሥልጠና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በቀለ ምሥጋናው ወጣቶችን በማደራጀት በከተማዋ የልማት ሥራ እንዲሳተፉ በማድረግ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ 5 ሺህ ለሚኾኑ ወጣቶች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል። ወደ ኢንተርፕራይዝ ያደጉ መኖራቸውንም አንስተዋል።
ሴቶችን እና አካል ጉዳተኞችን ከውድድር ጀምሮ በማበረታታት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረጋቸውንም ጠቅሰዋል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ማስተዋል አሰሙ መሪዎች እና ኅብረተሰቡ እጅ እና ጓንት ኾነው በመሥራታቸው ሰላሙንም ልማቱንም መፈጸም ተችሏል ብለዋል።
ለአዴት የሚያስፈልገው ሰላም ነው ያሉት ኀላፊው ሰላም ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የማኅበራዊ እና የምጣኔ ሃብት ልማት አስፈላጊ መኾኑንም ገልጸዋል።
የተጀመረው ልማት እና የሚታየው ሰላም በዘላቂነት እንዲሰፋ በተሳሳተ መንገድ የወጡ ልጆቹን ወደ ሰላሙ እንዲመልስ ኅብረተሰቡን አደራ ብለዋል።
በሌሎች አካባቢዎች ጫካ የወጡ ወንድሞች በሰላም እየገቡ በሰላም እየኖሩ መኾኑን የጠቀሱት ኀላፊው የአዴት እና አካባቢው ማኅበረሰብም ለሰላም ጠንክሮ እንዲሠራ አሳስበዋል።
የተጀመሩ ልማቶችም እንዲጠናቀቁ ኅብረተሰቡ መሪውን በመደገፍ ልማቱን ማሳደግ እንደሚገባው ነው የተናገሩት።
ልማት እንዲሠራ ያስተባበረውን መሪ፣ ሕዝቡን እና አካባቢውን ሰላም እንዲያገኝ ላደረገው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን