
ባሕር ዳር: ሰኔ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር እንጅባራ ከተማን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች ጽንፈኝነትን የሚያወግዝ እና መንግሥት እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር ርምጃ የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰልፎች ተካሂደዋል።
በእንጅባራ ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፉ የከተማው ነዋሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ፈረሰኞች እና ሌሎችም የብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው በክልሉ ብሎም በብሔረሰብ አስተዳደሩ ላለፉት ሁለት ዓመታት በዘለቀው ግጭት ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳቶች ደርሰዋል ብለዋል።
በግጭቱ በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት እንዲወድሙ ምክንያት ኾኗል ነው ያሉት። በተጠጨማሪ የዜጎች ነጻ የእንቅስቃሴ ተገድቦ መቆየቱን አንስተዋል።
መንግሥት ከፀጥታ መዋቅሩ እና ከሰላም ወዳዱ ሕዝብ ጋር ተቀናጅቶ ባካሄደው ሕግ የማስከበር ርምጃ በብሔረሰብ አስተዳደሩ አንፃራዊ ሰላም እየሰፈነ እንደመጣም ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል።
የአዊ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን በመቆም ለሰላም ያሳየው ቁርጠኝነት ለሌላው አካባቢ ትምህርት የሚሰጥ መኾኑን አቶ ቴዎድሮስ አንስተዋል። በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ሕዝቡ ሕዝባዊ ደጀንነቱን አጠናክሮ ማስቀጠል አለበት ብለዋል።
ነፍጥ አንግበው ጫካ የገቡ ወገኖች በአፈሙዝ የሚፈታ ችግር እንደሌለ ተረድተው መንግሥት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ በመቀበል እንዲመለሱ ሲሉ ዋና አስተዳዳሪው ጥሪ ማቅረባቸውን ከአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን መምሪያ ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!