
አዲስ አበባ: ሰኔ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዶክተር አምባቸው መኮንን 6ኛ ዓመት የሰማዕታትነት መታሰቢያ በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዮኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በችግኝ ተከላ እና በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
በ6ኛ ዓመት መታሰቢያው ላይ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የዶክተር አምባቸው ፍውንዴሽን የቦርድ አባላት እና ቤተሰቦቹ ተገኝተዋል። የመታሰቢያ ዝግጅቱም “ያለፈውን ማክበር የወደፊቱን መትከል” በሚል መሪ መልዕክት ነው የተካሄደው።
በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል መልካም ሥራ እና ራዕይ የነበራቸው ሰዎች ሲያርፉ ራዕያቸው የተሳካ እንዲኾን በትብብር ልንሠራ ይገባል ብለዋል። ዶክተር አምባቸው መኮንን ለሀገር ልማት ራዕይ እና ዕቅድ የነበራቸው መኾኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ በቀጣይም የተቋቋመው ፋውንዴሽን በትምህርት እና በሰላም ዙሪያ በሰፊው ይሠራል ነው ያሉት።
በፕሮግራሙ ላይ የዶክተር አምባቸው መኮንን ፍውዴሽን ዋና ሥራ አሥኪያጅ መዓዛ አምባቸው ዶክተር አምባቸው መኮንን በሕይዎት እያሉ ለአረንጓዴ ልማት ያላቸውን ራዕይ የተሳካ ለማድረግ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
በስማቸው የተቋቋመው ፋውንዴሽን 5ኛ ዓመቱን እንዳስቆጠረ የተናገሩት ሥራ አሥኪያጇ ፍውዴሽኑ በሥራ ላይ ነው፤ በቀጣይም በሰፊው ተደራጅቶ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በመሰማራት ለልማት የሚተጋ ተቋም ይኾናል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ራሔል ደምሰው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን