
ባሕር ዳር: ሰኔ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በበርካታ አካባቢዎች የሚገኙ የማኀበረሰብ ክፍሎች በየዓመቱ በክረምት ወቅት የጎርፍ ሰለባ እንደሚኾኑ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የምንሰማው ሐቅ ነው።
ጎርፍ በሚያስከትለው ጉዳትም ድልድዮች እየተደረመሱ ትራፊኩ ይስተጓጎላል፤ እንስሳት በደራሽ የጎርፍ ሙላት ይወሰዳሉ፤ እፅዋት ከሥራቸው ይመነገላሉ፤ ቤቶች ይፈርሳሉ፤ የኤሌክትሪክ ገመዶች ተቆርጠው ይወድቃሉ፤ ቡቃያዎች በደለል ሲጠፉ፣ ማሳዎች ሲሸረሸሩ እና ኢንዱስትሪዎች በመብራት እጦት ሥራቸው ሲስተጓጎል እንታዘባለን።
“ነገር በምሳሌ፤ ጠጅ በብርሌ ያምራል” እንዲሉ አበው ሐሳቤን በሰው ተኮር ምሳሌዎች ላስደግፈው።
“ጎሽ መጠጥ” የወራጅ ወንዝ ስም ነው። ይህ ወራጅ ወንዝ የሚከሰተው በክረምት ወቅት ብቻ ነው። የጎሽ መጠጥ መነሻ ደግሞ ከባሕር ዳር በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው የመሸንቲ ከተማ ዙሪያ ገባ ነው። ወንዙ በክረምት ግሳንግሱን ይዞ መዳረሻውን ጣና ሐይቅ ያደርጋል።
ከፊት ለፊቱ ደግሞ ጉዶ ባሕር እና ጋርባስ የሚሰኙ ክረምት ተኮር ኩሬዎች አፋቸውን ከፍተው ይጠብቁታል። እነዚህ ኩሬዎች በባሕር ዳር ከተማ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ላይ ይገኛሉ። በጎሽ መጠጥ ወንዝ ገባርነት የኩሬው ውኃ ጢም ብሎ ሲሞላ በጣና ክፍለ ከተማ ሥር የሚገኙትን የሽምብጥ፣ ሕዳሴ እና ምድረ ገነት ቀበሌዎችን እያጥለቀለቀ ወደ ጣና ሐይቅ ይፈሳል።
በጉዞውም በርካታ የማኀበረሰብ ክፍሎችን እያፈናቀለ፣ ንብረት እያወደመ፣ እንቅስቃሴን እያስተጓጎለ የጣና ሐይቅን ማሳረጊያው ያደርጋል።
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ እናት “ኧረ እናንተ! ሰው አልሚ፤ ሰው አጥፊም ነው። የድሮ ጎርፍ’ኮ እንደ ጨዋ መንገደኛ ፈሩን ብቻ ይዞ ነበር የሚጓዘው።
አኹንማ እንደ ተልከስካሽ ውሻ በየሰፈሩ መዞር ጀምሯል። ለነገሩ የመውረጅያ ቱቦው ሲደፈንበት፣ መንገዱ በድንጋይ ክምር እና አሸዋ ቁልል ሲዘጋበት እሱ ምን ያድርግ?!” በማለት ለጎርፍ መከሰት ምክንያቱም የመፍትሔው አካልም ሰው መኾኑን ጠቁመዋል።
የወይዘሮዋ ሐሳብ ከባሕር ዳር ከተማ ውጭ ያሉ አካባቢዎችንም የሚመለከት ኾኖ ነው ያገኘሁት። የጎሽ መጠጥ ወንዝ፣ የጉዶ ባሕር እና የጋርባስ ኩሬዎች እንዲኹ መውረጃ መንገዳቸው በመደፈኑ ነው አካባቢን የሚያጥለቀልቁት። ሕዝብን ከቀየው የሚያፈናቅሉት። ንብረት የሚያወድሙት አልሁ ለራሴ።
ወዲህ በየዓመቱ የሚፈጠረው ጎርፍ ኮለል ብሎ እንዲወርድ ዜጋ ተኮሩ መንግሥት ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ ቦይ ይገነባል።
ቦዩ በተገነባበት ዓመትም ጎርፍ ሲንፎለፎል ተመልክቶ ያልተደሰተ ጤነኛ ሰው ያለ አይመስለኝም።
ይሁንንና “ሰው አልሚ፤ ሰው አጥፊ” እንዳሉት ወይዘሮዋ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ኀብረተሰቡ የጎርፍ ማስወገጂያ “ዲቾችን” እና ቱቦዎችን በልዩ ልዩ ቁሶች እየደፈነ ራሱን በራሱ ለችግር ሲዳርግ እና ዳፋውን ለሌሎች ወገኖች ሲያስተጋባ አስተውያለሁ።
ለምሳሌ ባለፈው ዓመት በባሕር ዳር ከተማ ጣና ክፍለ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ የጎርፍ ማፋሰሻ ቦዮች ለግንባታ ወይም ለንግድ ተብሎ በተደፋ አሸዋ፣ ድንጋይ፣ አፈር እና በሌሎችም ቁሶች በመደፈናቸው ጎርፍ መውረጂያ በማጣቱ አካባቢን ሲያጥለቀልቅ፣ በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ሲያስከትል ታዝቤያለሁ።
በመሐል ከተማ የሚገኙ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትም ጨለማን ተገን አድርገው ደረቅ ቆሻሽያ የሚያስወግዱት ለፍሳሽ ቆሻሽያ ማስወገጅያ ብቻ ተብሎ በተሠራ ቦይ ውስጥ ነው። ያሳዝናል!
ቦዩ በደረቅ ቆሻሽያ እየተደፈነም ጎርፍ መውረጃ ሲያጣ በአስፋልቱ ላይ ለመውጣት ወይም ወደ መኖሪያ ቤቶች ለመግባት ሲገደድ አይተናል። በመኾኑም በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ሲደርስም እንዲኹ ታዝበናል።
ከባሕር ዳር ወጣ ስንል በየዓመቱ ለጎርፍ ተጠቂ የኾኑ የክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ለአብነት ከደቡብ ጎንደር እንደ ፎገራ፣ ሊቦ ከምከም፤ ከሰሜን ወሎ እንደ ወልዲያ፤ ከደቡብ ወሎ እንደ ደሴ ዙሪያ፤ ከሰሜን ጎጃም እንደ አንዳሳ፣ በጣና እና ዓባይ ዙሪያ እንዲኹም ሌሎች ከተሞችም ነገን ዛሬ ካልሠሩ በጎርፍ መጎዳታቸው ሳይታለም የተፈታ ሐቅ ነው።
ላለፈ ክረምት ቤት ባይሠራም ታዲያ በመጭው ክረምት በዝናብ ላለመጎዳት ተብሎ ቤት እንደሚሠራው ሁሉ ለጎርፍ ተጠቂ የኾኑ የማኀበረሰብ ክፍሎችም ራሳቸውን ከደራሽ ጎርፍ ለመጠበቅ የመከላከያ ዘዴዎችን ከወዲኹ ማጠናከር አለባቸው።
የውኃ መፋሰሻ ቱቦዎችን በአግባቡ ማፅዳት፣ የአረንጓዴ ዓሻራ ሥራዎችን ማስፋፋት፣ አዳዲስ ቦዮችን መገንባት ግድ ይላቸዋል ባይ ነኝ፡፡ እንዲህ ሲያደርጉም ነገ ላይ ሊከሰት እና ጉዳት ሊያደርስ የሚችልን ጎርፍ ዛሬ ቀድመው ሊከላከሉት ይቻላቸዋል።
የከተማ አሥተዳዳሪዎችም የጎርፍ ተጋላጭ ቦታዎችን አስቀድመው በመለየት ኀብረተሰቡ በባለቤትነት መንፈስ እንዲያፀዳቸው ከፊት ኾነው የመሪነት ሚናቸውን በመወጣት ነገ ላይ ሊከሰት የሚችልን የጎርፍ አደጋ ዛሬ በሚሠራ መልካም ተግባር መቅደም ይኖርባቸዋል።
ውኃ በሚያቁሩ አካባቢዎች የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለጎርፍ የመጋለጥ ዕጣቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ አደጋው በየትኛውም ቅፅበት ሊያጋጥማቸው ይችላል።
በዚህም በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ይደርሳል፡፡ ስለዚህ “ሳይቃጠል በቅጠል”እንዲሉ ለጎርፍ መጥለቅለቅ ምክንያት የኾኑ ነገሮችን ሁሉ ከወዲኹ በደቦ ማስወገድ ግድ ይላል።
የተገነቡትን የጎርፍ ማፋሰሻዎች በአግባቡ መያዝ፣ መጥረግ፣ መክፈት፣ አዲስ መገንባትም ግድ ይላቸዋል። ነገን ዛሬ መሥራት ማለትም ይኽው ነው።
በሙሉጌታ ሙጨ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን