የእንጅባራ ከተማ ነዋሪዎች ፅንፈኝነትን የሚያወግዝ እና መንግሥት እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር ርምጃ የሚደግፍ ሰልፍ አካሂደዋል።

27

እንጅባራ: ሰኔ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በድጋፍ ሰልፉ የከተማው ነዋሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ፈረሰኞች እና ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
በሰልፉ ፅንፈኝነትን እናወግዛለን፣ ሰላም እንፈልጋለን፣ ልጆቻችንን ማስተማር እንሻለን፣ ጦርነት ይብቃ፣ የጥይት ድምፅ መስማት አንፈልግም የሚሉና ሌሎችም መልዕክቶች ተስተጋብተዋል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው ለሰልፈኞቹ ባስተላለፉት መልዕክት በክልሉ ላለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ የተፈጠረው ግጭት ካደረሰው ሰብዓዊ ጉዳት ባሻገር ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በማስተጓጎል የክልሉን እድገት እየገታ መኾኑን ነው ብለዋል።

ግጭቱ በርካታ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ አፈናቅሏል፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያሚያዊ ተቋማት እንዲወድሙ አድርጓል፣ የዜጎች የእንቅስቃሴ እንዲገደብ ኾኗልም ነው ያሉት።
የማኅበረሰቡን የቆዩ የአብሮነት እሴቶች እንዲሸረሸሩ በማድረግ መጠራጠርና ሥርዓት አልበኝነት እንዲሰፋ አድርጓልም ብለዋል።

የፀጥታ መዋቅሩ ከሰላም ወዳዱ ማኅበረሰብ ጋር ተቀናጅቶ በሠራቸው ሥራዎች በብሔረሰብ አሥተዳደሩ አንፃራዊ ሰላም እየሰፈነ መምጣቱንም ገልጸዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዘላቂ ሰላም ለማጽናት ኅብረተሰቡ ማንነትን ከአብሮነት ጋር አሰናስሎ በመጓዝ ለሰላም ያለውን አጋርነት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም አስገንዝበዋል።
ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ወገኖች በግጭት የሚፈታ ችግር ባለመኖሩ ለሰላማዊ ውይይት ቅድሚያ እንዲሰጡ እና መንግሥት ያቀረበውን የሰላም አማራጭ እንዲቀበሉም ጥሪ አስተላልፈዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ ክላስተር አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ(ዶ.ር) ካጋጠመን ቀውስ መውጫ መንገዱ የሰላም አማራጭን መከተል እና ለሰላም በአንድነት ዘብ መቆም ነው ብለዋል።
በተሳሳተ መንገድ የሚጓዙ ወገኖች እንዲመለሱ የሃይማኖት አባቶች ሰላምን የመስበክ ሥራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በልዩ ልዩ መርሐ ግብሮች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ።
Next articleበአንከሻ ጓጉሳ ወረዳ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።