ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በልዩ ልዩ መርሐ ግብሮች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ።

23

ደብረ ብርሃን: ሰኔ 15/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ደብረ ብርሃን የኒቨርሲቲ በስምንት ኮሌጆች፣ በ39 የትምህርት ዓይነቶች የሠለጠኑ 1 ሺህ 108 የመጀመሪያ ዲግሪ እና 251 የድህረ ምረቃ ተማሪዎችን አስመርቋል። የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት አስማረ መለሰ (ዶ.ር) ተመራቂ ተማሪዎች ሙሉ ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም በዕውቀት፣ በክህሎት፣ በአመለካከት እና በሥነ ምግባር የበቁ መኾናቸውን ገልጸዋል። ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ሙሉ ኾነው እንዲወጡ መምህራን ያለመሰልቸት ላደረጉት ድጋፍ እና ክትትል ዶክተር አስማረ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በተሰጠው ተልዕኮ መሠረት የመማር ማስተማር ሥራን በመተግበር፣ ችግር ፈቺ ምርምር በማድረግ እና የፈጠራ እና ቴክኖሎጂ ሥራዎች በመደገፍ ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ ይቀጥላል ብለዋል። ዩኒቨርስቲው ለሀገር ዕድገት ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተ መኾኑንም ጠቅሰዋል። ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በተለያዩ የትምህርት መስኮች የቀሰሙትን እውቀት፣ ያካበቱትን ክህሎት እና ተሞክሮ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለሀገር እና ለሕዝብ በሚጠቅም አግባብ ተግባራዊ እንዲያደርጉ የአደራ ቃል ሰጥተዋል።

የበለጠ ብቁ እና ተወዳዳሪ በመኾንም በቅንነት፣ በታማኝነት እና በታታሪነት እንዲያገለግሉም አሳስበዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የኢትዮጵያ ኅበረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጀኔራል ዳይሬክተሩ ዶክተር መሳይ ኃይሉ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።
ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን ሲያስመርቅ የአሁኑ ለ18ኛ ዙር መኾኑ ነው።

ዘጋቢ፦ ደጀኔ በቀለ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።
Next articleየእንጅባራ ከተማ ነዋሪዎች ፅንፈኝነትን የሚያወግዝ እና መንግሥት እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር ርምጃ የሚደግፍ ሰልፍ አካሂደዋል።