በዘንድሮው የክረምት ወቅት ለሰብል ምርት የማይውል አንድም መሬት መኖር እንደሌለበት አቶ ብናልፍ አንዷለም ተናገሩ።

335

የፌዴራልና የአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ የሥራ ኃላፊዎች በሰሜን ሸዋ ዞን የግብርና ሥራዎችንና ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝተዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በብዙ ዘርፎች ተጽዕኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡ በመጪው የመኸር እርሻ እና በሰብል ምርታማነት ላይ ሊያደርስ የሚችለው ተጽዕኖም ከስጋቶች መካከል ነው። ይህንን ለመቋቋም ደግሞ ሁሉንም መሬቶች በሰብል መሸፈንና የአርሶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንደሚገባ በሀገር ደረጃ አቅጣጫ ተቀምጧል። ሥራውን ለማበረታታትም የፌዴራልና የክልል የብልጽግና ፓርቲ የሥራ ኃላፊዎች በሃገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የመስክ ምልከታ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ዛሬ ግንቦት 20/2012 ዓ.ም ደግሞ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምልከታ አካሂደዋል።

የብልጽና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷም ይህ ወቅት እጅግ ፈታኝ በመሆኑ ከዚህ ፈተና ማምለጥ የሚቻለው የጥንቃቄ ርምጃዎችን በመተግበር ነው ብለዋል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ በግብርና ሥራው ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽዕኖ ቀድሞ በመረዳት ሁሉም ርብርብ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ “በዘንድሮዉ የመኸር ወቅት የማይታረስ አንድም መሬት መኖር የለበትም፤ እንዲያውም ካሁን በፊት ሳይታረሱ ጾም ሲያድሩ የነበሩ መሬቶች ሁሉ መታረስ ይገባቸዋል” ብለዋል አቶ ብናልፍ፡፡

የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ለግብርና ሥራው ከፍተኛ ርብርብ ካልተደረገ የኮሮና ወረርሽኝ ከሚያስከትለው ጣጣ ባለፈ ረሃብም ሊከሰት ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ነው አቶ ብናልፍ ያስረዱት፡፡ ከመደበኛው የእርሻ ሥራ ባሻር በከተማ ግብርና ሰፊ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን እና አካባቢው በመስኖ ሥራውና በአምራች ኢንዱስትሪው ላይ እተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ለሌሎች አካባቢዎችም በአርዓያነት የሚጠቀሱ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

በጉብኝቱ የተሳተፉት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው የክልሉ መንግሥትና ፓርቲው የግብርናን ጉዳይ መሠረታዊ ተግባር አድርገው እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የግብዓት አቅርቦት ችግሩን ለመቅረፍ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ በዚህ የመኸር እርሻ ወቅት ከ 6 ሚሊን በላይ ኩንታል ማዳበያ እንደሚያስፈልግ የተናገሩት አቶ አገኘሁ ሥርጭቱም የተሻለ መሆኑን ለአብመድ ገልጸዋል፡፡

“በተወሰኑ የምርጥ ዘር አይነቶች ላይ እጥረት አለ፤ በተለይም ሊሙ የተባለው የበቆሎ ዘርና የቢራ ገብስ ዝርያዎች ላይ እጥረት መኖሩን አረጋግጠናል፡፡ ይህን ለመቅረፍም ከክልሎች ጋር እየተነጋገርን ችግሩ እንዲፈታ እያደረግን እንገኛለን” ነው ያሉት አቶ አገኘሁ፡፡ በዘላቂነት ከችግሩ መውጣት የሚቻለው ግን የዘር ብዜት ላይ በሚገባ ሲሠራ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ለመኸር እርሻ ከሚደረገው ሥራ ባሻገር በአማራ ክልል በዘንድሮው ክረምት ከ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከልም ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ዘጋቢ፦ ኤልያስ ፈጠነ-ከደብረ ብርሃን

Image may contain: one or more people, outdoor and closeup
Previous articleበረኸት ወረዳ አዋሳኝ አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡
Next articleበኩር ጋዜጣ ግንቦት 24/2012 ዓ/ም ዕትም