“የ25 ዓመታት ዕቅዱ የክልሉን ሕዝብ ወደ በለጸገ ደረጃ ማሻገር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው” ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)

24

ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የአማራ ክልል የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም የልማት ዕቅዶች ዋነኛ ባሕሪ የሕዝብን መሠረታዊ ችግሮች መፍታት የሚያስችል ግቦችን ማስቀመጥ ነው ብለዋል። የአማራ ክልል በሁለቱ ጉዳዮች የሚገለጹ ተደጋጋሚ ችግሮች አሉበት ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ የድህነት እና የግጭት አዙሪት የክልሉ ችግሮች መኾናቸውን አንስተዋል።

የግጭት እና የድህነት አዙሪቶች ለረጅም ጊዜ የቆዩ እና አሁን ክልሉ ላለበት የጸጥታ ችግር መሠረታዊ መነሻ መኾናቸውን ነው የተናገሩት። “የክልሉ የ25 ዓመታት የአሻጋሪ እና የቁጭት ዕቅድ ለዘመናት የዘለቁ የድህነት እና የግጭት አዙሪቶችን ትርጉም ባለው ደረጃ በመፍታት የክልሉን ሕዝብ ወደ በለጸገ ደረጃ ማሻገር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው” ብለዋል።

የ25 ዓመታቱ ዕቅድ ከሌሎቹ ዕቅዶች የተለየ እና የክልሉን ሕዝብ ችግር የገመገመ መኾኑን አንስተዋል። ካሁን ቀደም የነበሩ ዕቅዶች በተገቢው መንገድ የማይታቀዱ፣ በተገቢው መንገድ ያልተመሩ እና ክትትል ያልተደረገባቸው ነበሩ ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ዛሬን ብቻ ሳይኾን ነገን ታሳቢ በማድረግ ትውልዱን ማነጽ እና ማሻገር ይገባል ነው ያሉት።

የ25 ዓመታቱ ዕቅድ የሚደርስባቸው ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ግቦች እንዳሉትም ተናግረዋል። የክልሉን ምጣኔ ሀብት በላቀ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ መኾኑንም አመላክተዋል።

ትውልድን ማነጽ ታሳቢ ያደረገ ዕቅድ መኾኑንም ገልጸዋል። በምጣኔ ሃብት የበለጸገ ማኅበረሰብ፣ ባሕሉን የጠበቀ፣ በትምህርት የላቀ ትውልድ፣ በላቀ ቴክኖሎጂ ላይ ተመሥርቶ ሥራዎችን የሚሠራ፣ ሥልጡን የፖለቲካ ባሕልን የሚከተል ማኅበረሰብ እንዲፈጠር ይፈልጋል ነው ያሉት። የሕዝብን አኗኗር የሚቀይር ዕቅድ ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ነገር ግን ዕቅዱ ስለታቀደ ብቻ የሚሳካ አይደለም፣ የትውልድ ዕቅድ ስለኾነ የሚፈጸመውም በትውልድ ነው ብለዋል። ዕቅዱ እንዲፈጸም ክትትል እና ድጋፍ የሚያደርግ መሪ እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት።

መሪዎች ከሕዝብ ጋር በመቀናጀት መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አንስተዋል። በ25 ዓመታቱ ዕቅድ እንዲሳኩ የተቀመጡ ጉዳዮችን ለይቶ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። የክልሉን ሰላም እና የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ የቅድሚያ ቅድሚያ ጉዳይ መኾኑንም ገልጸዋል።

ዕቅዱ ሦስት ደረጃዎች አሉት ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ የማገገም፣ የመመንጠቅ እና የመበልጸግ ደረጃዎች አሉት፣ በማገገም ደረጃ አሁን የገጠመንን የሰላም እና የጸጥታ ችግር መፍታት፣ በሰላም የጸጥታ ችግር የወደሙ መሠረተ ልማቶችን ማስተካከል ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የማኅበረሰብ እሴቶችን በማጠናከር እና በመጠበቅ በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ መፍጠር ሌላኛው ጉዳይ መኾኑን ገልጸዋል። ክልሉ የዳበረ ባሕል፣ ወግ፣ እሴት አለው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ነገር ግን አሁን ላይ የዳበሩ እሴቶች እየተሸረሸሩ መጥተዋል፣ ለክልሉ ሁለንተናዊ ዕድገት በጎ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ እሴቶችን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።

በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ለሀገር ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል። ትውልድ በሥነ ምግባር ሲታነጽ የሀገር፣ የሕዝብ እና የፍትሕ ፍቅር እንደሚኖረውም ገልጸዋል። የሀገር፣ የሕዝብ እና የፍትሕ ፍቅር ያለው ትውልድ ደግሞ ለሕዝብ ትስስር እና አንድነት አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ሳይንሳዊ ዕውቀትን መጠቀም ለምጣኔ ሀብት ግንባታ አስፈላጊ መኾኑንም ተናግረዋል። ሳይንሳዊ ዕውቀትን መሸከም የሚችል ትውልድ መገንባት እንደሚጠበቅም አንስተዋል።

በቴክኖሎጂ ላይ የተመሠረተ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባም ገልጸዋል። የክልሉ መሠረታዊ ችግሮችን በጥልቀት የተረዳ እና በቁርጠኝነት የሚሠራ የፖለቲካ መሪ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። መሪ በአንድ ጊዜ የሚፈጠር ሳይኾን በቅብብሎሽ የሚፈጠር ነው ብለዋል። የተፈጠሩ ችግሮች በአንድ ጊዜ የተፈጠሩ ሳይኾኑ ለዘመናት የመጡ ናቸው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ድርብርብ የኾኑ ችግሮችን ለመፍታት ደግሞ አሻጋሪ ዕቅድ ያስፈልጋል ነው ያሉት። የታቀደው ዕቅድ ሀገራዊ ዕቅዶችን ታሳቢ ያደረገ፣ የአተገባበር መንገድን ያመላከተ፣ የክልሉን አቅም በተገቢው የለየ መኾኑንም ገልጸዋል።

አሁን ያለንበትን የጸጥታ ችግር ዕቅዱ እንዳይሳካ ያደርጋል ብለው የሚሰጉ አሉ ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ያደጉ ሀገራት ተመንጥቀው የወጡት ችግር በገጠማቸው ጊዜ መኾኑን መረዳት ይገባል ነው ያሉት። በርካታ ሀገራት ወደ ዕድገት የገሰገሱት ከችግር በኋላ መኾኑንም አንስተዋል። በአማራ ክልል የታቀደው ዕቅድ ከችግር በኋላ ወደ ዕደገት የወጡትን ተሞክሮ የወሰደ ነው ብለዋል።

በመሪዎች ዘንድ የተፈጠረው ቁጭት ለዕቅዱ መሳካት ሁነኛ መደላድል መኾኑንም ገልጸዋል። ለችግሮች ከወትሮው የተለየ አረዳድ እንዳለም አንስተዋል። ክልሉ ያለው ሰፊ ጸጋ ለዕቅዱ መሳካት ትልቅ አቅም መኾኑንም ተናግረዋል። ዕቅዱ ውጤታማ እንዲኾን እስከዛሬ ከነበሩ የዕቅድ ክትትል እና ግምገማ ለየት ያለ እንደሚኾንም አመላክተዋል። ክትትሉ እና ድጋፉ ጸጋዎችን መሠረት ያደረገ መኾኑንም አብራርተዋል።

ድጋፍ እና ክትትሉ ተቋማዊ እና ሕጋዊ በኾነ መልኩ እንደሚመራም አንስተዋል። የአማራ ሕዝብ እና መንግሥት የኾነው ዕቅድ በትውልዶች መቀያየር ወደኋላ እንዳይቀር ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል። ዕቅዱ ወደኋላ እንዳይል ተገቢው ጥንቃቄ እንደሚደረግም ገልጸዋል።

ተቋማት ከ25 ዓመታት ዕቅዱ የተቀዳ ዕቅድ እንዲያቅዱም አሳስበዋል። ሕዝቡ ዕቅዱ ተፈጻሚ እንዲኾን ተሳትፎውን እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል። ባለሀብቶችም የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ነው ያስገነዘቡት። ግጭት ላይ ጊዜያችን ከምናጠፋ በአንድነት እና በመተባበር ወደ ተሟላ ዕድገት መጓዝ አለብን ነው ያሉት። በግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች ከግጭት በመውጣት እና ሰላማዊ መንገድን በመምረጥ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleለኅብረተሰቡ የጤና አደጋ የኾኑ እገታ፣ ጠለፋ እና ዘረፋን በተቀናጀ መንገድ ለመከላከል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ተጠየቀ።
Next articleየአዴት ከተማ አስተዳደር በበጀት ዓመቱ ያከናዎናቸውን የመሰረተ ልማት ሥራዎች ዛሬ ያስመርቃል።