
ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና አደጋ በኾኑ ጉዳዮች ላይ ከክልሉ የሥራ ኀላፊዎች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
በውይይቱ ሁለት ጥናቶች የቀረቡ ሲኾን በንብረት ዝርፊያ፣ ጠለፋ እና ሰውን ማፈን ላይ የተደረገ ጥናት አንዱ ነው።
የጥናቱ አቅራቢ የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጤና ልማት ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር አዳነ ንጉሴ እንዳሉት ጥናቱ ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ማቆስ፣ ደብረ ብርሃን እና ደሴ ከተሞች ላይ ያተኮረ ነው።
በጥናቱ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተካትተዋል። በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ሁኔታ በመጠቀም ጠለፋ፣ ዝርፊያ እና ሰውን አስገድዶ ማፈን ባልተለመደ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
ሌላኛው በውይይቱ የቀረበው ራስን ማጥፋት ላይ የተደረገ ጥናት ነው። የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የአዕምሮ ጤና፣ የሥነ ልቦና እና ማኅበራዊ ድጋፍ ባለሙያ ቃልኪዳን ኃይሌ ራስን ማጥፋት በክልሉ መጨመሩን ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ የአዕምሮ ጤና ወታወክ ዋነኛው ምክንያት ኾኖ ተቀምጧል። ጾታዊ ጥቃት፣ ጠለፋ፣ ዝርፊያ እና የቤተሰብ ግንኙነት ችግር ራስን ለማጥፋት ሌላኛው ምክንያት መኾኑ ነው የተገለጸው።
የችግሩ ተጠቂ ከኾኑት ውስጥ ደግሞ ከ11 እስከ 29 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች 78 በመቶ የሚኾነውን ድርሻ እንደሚወስዱ ነው ያብራሩት።
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ በወቅታዊ የኅብረተሰብ ጤና ችግሮች ላይ ጥናቶችን በማጥናት ለውሳኔ እያቀረበ ይገኛል።
በሰሜኑ ጦርነት የደረሰውን ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት በማጥናት የመልሶ ማቋቋም ሥራ እየተሠራ መኾኑንም በማሳያነት አንስተዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታትም በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት መድረሱን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ በግጭቱ የደረሰውን ሰብዓዊ ጉዳት ለማወቅም በኢንስቲትዩቱ ጥናት መደረጉን ገልጸዋል።
በጥናቱም እገታ፣ ጠለፋ፣ ዘረፋ እና ራስን ማጥፋት የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ኾኖ መገኘቱን ገልጸዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ ማኅበረሰቡ፣ የጤና ተቋማት፣ የመንግሥት ተቋማት እና ዓለም አቀፍ ረጅ ድርጅቶች በትብብር ሊሠሯቸው ይገባል ያሏቸውን ዋና ዋና ጉዳዮችን አስቀምጠዋል።
ከእነዚህም ውክጥ ማኅበረሰቡ ራሱን በማደራጀት እገታ እና ዘረፋ የሚፈጽሙ አካላትን ሊከላከል ይገባል። የሥነ አዕምሮ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ፈጥኖ ወደ ጤና ተቋማት ማድረስ ይገባል ነው ያሉት።
በሰው ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ኬሚካሎችን በሕግ መቆጣጠር ይገባልም ብለዋል። አምራች እና ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን ማስፋፋትም ይገባልም ብለዋል። ለወጣቱ የሥራ ዕድል መፍጠር ይገባልም ነው ያሉት።
የጤና ተቋማት እና ጤና ላይ የሚሠሩ ድርጅቶች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና የሃይማኖት ተቋማት የሥነ አዕምሮ እና የሥነ ልቦና ትምህርት ሊሰጡ ይገባል።
የሚዲያ ተቋማትም ከኢንስቲትዩቱ ትክክለኛውን መረጃ በመውሰድ ለማኅበረሰቡ እንዲያደርሱም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን