
ደሴ: ሰኔ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደቡብ ወሎ ዞን አሥተዳደር በደሴ ከተማ ከሚኖሩ የዞኑ ተወላጅ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቷል።
የደቡብ ወሎ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፓለቲካ ዘርፍ ኀላፊ መሐመድ አሊ የመወያያ ጽሑፍ አቅርበዋል።
በመወያያ ጽሑፉም “በዞኑ በጽንፈኞች ምክንያት ሰብዓዊ ቀውስ ፣ የአካል እና የሥነ ልቡና ጉዳት፣ እገታ እና የተለያዩ ችግሮች ማኅበረሰቡ ላይ ደርሰዋል” ብለዋል።
የጽንፈኛው ቡድን በዞኑ ኢንቨስትመንት እንዲዳከም አድርጓል ነው ያሉት። በዞኑ ስድስት የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወንድማቸውንም ገልጸዋል።
በጽንፈኛ ኀይሎች ምክንያት በዞኑ 43 አምቡላንሶች መውደማቸውን፣ 687 ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ውጭ እንዲኾኑ አድርጓል ነው ያሉት። መምህራንም በጽንፈኞች ከእስራት እስከ ግድያ ድረስ እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል።
ችግሩን ለማስወገድ የሕዝብ ውይይቶች በተደጋጋሚ መካሄዳቸውንም ገልጸዋል። በተካሄዱት ውይይቶችም የዞኑ ሕዝብ ሰላም እንዲሰፍን እንደሚፈልግ እና ለሰላም እንደሚተባበርም ገልጿል ነው ያሉት።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም ሰላም ያስፈልጋል ብለዋል።የዞኑ አሥተዳደር የጀመረውን ሰላም የማስከበር ሥራ ማጠናከር ያስፈልጋል፤ ለሰላም መደፍረስ አንዱ ምክንያት የመልካም አሥተዳደር ችግር በመኾኑ ይህን ማስተካከል እና ሕዝቡ የሚጠይቀውን የልማት ጥያቄ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የተማሩ እና በከተማ የሚኖሩ ጥቂቶች የፓለቲካ አጀንዳ በመፍጠር ራሳቸውን ደብቀው አርሶ አደሮችን ግን ፊት ለፊት እያጋፈጡ መኾናቸውን ተናግረዋል። ተልዕኮ አስፈፃሚዎች መኖራቸውን በሚገባ ተገንዝቦ ማክሸፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
ተሳታፊዎቹ የዞኑ አሥተዳደር መዋቅሩን በሚገባ ሊፈትሽ እንደሚገባም አንስተዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን ውይይቱ በደሴ ከተማ የሚኖሩ የደቡብ ወሎ ዞን ተወላጆች የጽንፈኛ ቡድኑ በገጠሩ ማኅበረሰብ ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ እንዲገነዘቡ ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ መኾኑንም ተናግረዋል።
አሰቀድሞም ቢኾን አንፃራዊ ሰላም የነበረበት ዞኑ የሰላም ሁኔታው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።
በደሴ ከተማ የሚኖሩ የዞኑ ተወላጆች የጸጥታ ችግሩ በዞኑ ማኅበረሰብ ላይ ያደረሰውን ግፍ ተገንዝበው ለሰላም ተባባሪ መኾን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን