“ጠቢብ ሰው ማለት የሚኖርበትን ማኅበረሰብ የሚያገለግል ነው” አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር)

22

ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሐ ግብሮች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።

ዩኒቨርሲቲው በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በሦስተኛ ዲግሪ መርሐ ግብሮች ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ 6ሺህ 174 ተማሪዎችን ነው ያስመረቀው።

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የከተማ እና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ.ር) ትምህርት ለአንድ ሀገር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች አውንታዊ ለውጥ ለማምጣት፣ ለሕዝብ ኑሮ መሻሻል ጉልህ ድርሻ እንደሚጫዎት አስረድተዋል።

ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ የሚለውን መሪ መልዕክት አንግባችሁ በጠቢባዊ አንደበት የዓባይን የጽናት መንፈስ በመሸከም ለለውጥ እና ለዕድገት ያለው ሁለገብ ቁርጠኝነት የሚንጸባረቅባችሁ የጥበብ ውጤቶች ናችሁ ብለዋል።

“ጠቢብ ሰው ማለት የሚኖርበትን ማኅበረሰብ የሚያገለግል ነው” ያሉት ኀላፊው ያገኛችሁትን ጥበብ በዲግሪ ተወስኖ የሚቀር ሳይኾን ችግሮችን በጥበብ የምትፈቱበት ነው ብለዋል።

ተመራቂዎች በቆይታቸው ያገኙት ጥበብ በማኅበረሰብ አቀፍ እና በቴክኖሎጅ ምርምሮች ለሚያደርጉት ጉዞ የሕይወት መሠረት እንደሚኾንም አመላክተዋል።

በየተመረቁበት የትምህርት መስክም የኢትዮጵያን እጣ ፈንታ በሚወስኑ ጉዳዮች ላይ ዋና አካል እንዲኾኑም አሳስበዋል።

ከፈተና ጋር ስኬት ይመጣል፣ በተግዳሮቶች እና በፈተናዎች ውስጥ አልፋችሁ ለዚህ የበቃችሁ ተመራቂዎች አንድነትን፣ አብሮነትን፣ ኅብረ ብሔራዊነትን የምታስከብሩ ትውልድ መኾን ይጠበቅባችኋል ብለዋል።

የዛሬው ደስታ እንዲዘልቅ እንደየሙያችሁ ለሰላም፣ ለዕድገት እና ለብልጽግና የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ማበርከት አለባችሁ ነው ያሉት።

እርስ በርሳችሁ ተከባብራችሁ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ለድርድር ሳታቀርቡ ሀገራችሁን በማስቀጠል ተጨማሪ ምርቃት የሚያስገኝ ሥራ መሥራት ይጠበቅባችኋል ብለዋል።

ባለውለታውን የዘነጋ ሀገሩን አያስታውስም እና ላስተማራችሁ ማኅበረሰብ አደራችሁን መወጣት አለባችሁ ነው ያሉት።

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መንገሻ አየነ (ዶ.ር ) ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ጥራት፣ ማኅበረሠብ ተኮር ሥራዎች እና ዓለም አቀፋዊነትን ባማከለ መልኩ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው የአፍሪካን የ2063 አጀንዳ እና የዘላቂ ልማት ግቦችን ታሳቢ አድርጎ የመማር ማስተማር ሥራውን እያከናወነ መኾኑንም ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ጥበብን፣ ጥራትን፣ ልህቀትን እና ዕውቀትን መሠረት አድርጎ ተምሳሌት ለመኾን እየሠራ እንደኾነም አመላክተዋል። ለፈጠራ ሥራዎችም ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።

ተመራቂዎች ካስቀመጡት ራዕይ ለመድረስ በብዙ ልፋት እና ድካም አልፈው ለዛሬ ስኬት እንደበቁት ሁሉ ያገኙትን ዕውቀት ተጠቅመው በትጋት ለማኅበረሰቡ እንዲያገለግሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleተመራቂ ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀት በመጠቀም ማኀበረሰቡን ማገልገል ይጠበቅባቸዋል፡፡
Next articleየጸጥታ ችግሩ በማኅበረሰቡ ላይ ያደረሰውን ግፍ በመገንዘብ ለሰላም ተባባሪ መኾን ይገባል።