
ደባርቅ: ሰኔ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ መርሐ ግብር ያሠለጠናቸውን ከ200 በላይ ተማሪዎችን ለሰባተኛ ጊዜ አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ሰባት ዓመታት ተማሪዎችን በዕውቀት በክህሎት እና በተለያዩ የሕይዎት ልምዶች ሲያበቃ ቆይቷል፡፡
በዚህ ዓመትም በተለያየ መርሐ ግብር ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች አስመርቋል፡፡
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስማማው ዘገየ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው ከመደበኛ የመማር ማስተማር ሥራው በተጨማሪ በጥናት እና ምርምር በማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር መርሐ ግብሮች የተለያዩ ተግባራት ማከናወኑን አስታውሰዋል፡፡
ትምህርት ከሕይዎት ዑደት ጋር ተሰናስሎ የሚሄድ ቀጣይነት ያለው ምዕራፍ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በቀጣይም ለበለጠ ስኬት መትጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የሰሜን ጎንደር ዞን ተወካይ ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሲቪል ሰርቪስ መምሪያ ኀላፊ ያሬድ አበበ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራው በተጨማሪ እየሠራቸው ለሚገኙ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች ዕውቅና በመስጠት አመሥግነዋል፡፡
ነገን የተሻለ ለማድረግ እና ዘመኑን በሚመጥን ሁለንተናዊ የለውጥ ጎዳና ለመራመድ ቅድሚያ ለትምህርት ዋጋ መስጠት ይገባል ብለዋል፡፡
ተመራቂ ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን ንድፈ ሃሳባዊ እና ተግባራዊ ዕውቀት በመጠቀም ማኀበረሰቡን በተገቢው መንገድ ማገልገል እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
የሰሜን ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ግዛቸው ሙጬ ሕግ ከዕውቀት እና ከክህሎት በተጨማሪ የስሜት ብልህነትን የሚጠይቅ መስክ መኾኑን ገልጸው ተመራቂ ተማሪዎቹ በአርቆ አሳቢነት ለፍትሕ እና ርትዕ ሊቆሙ እንደሚገባ ለሕግ ትምህርት ቤት ተመራቂ ተማሪዎች አሳስበዋል፡፡
የተመራቂ ተማሪ ወላጆች ልጆች መማር ባለባቸው ጊዜ ከተለያዩ ጫናዎች ነፃ ኾነው እንዲማሩ እና ለስኬት እንዲበቁ ቤተሰብ ኀላፊነቱን መወጣት እንደሚጠበቅበትም ተናግረዋል፡፡
ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተመራቂ ተማሪዎች በበኩላቸው ከመምህራን ክትትል እና ድጋፍ በተጨማሪ ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም እና የንባብ ባሕልን በማዳበር ለስኬት መብቃታቸውን ተናግረዋል፡፡
ትምህርት የለውጥ ሂደት እንጂ አለቀ የሚባል ጉዳይ አይደለም ሲሉም ነው ያብራሩት።
ቀጣይ የሕይዎት ምዕራፎችን በስኬት ለማጠናቀቅ ትጋት እና ትግስትን የሕይዎት መርህ ማድረግ እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን