
ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “አርቆ ማየት፣ አልሞ መሥራት” በሚል መልዕክት በአማራ ክልል ለተቋማት ዳይሬክተሮች የአሻጋሪ ዕድገት እና ዘላቂ ልማት ዕቅድ ዙሪያ ሥልጠና እየተሰጠ ነው።
የአማራ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ ኀላፊ ደመቀ ቦሩ (ዶ.ር) ለክልሉ የአሻጋሪ ዕቅድ ዝግጅት ወቅት ምሁራን እና የተቋም ዳይሬክተሮች መሳተፋቸውን ተናግረዋል። ነገር ግን ሁሉንም አካላት ለማሳተፍ አስቸጋሪ በመኾኑ ዕቅዱ ከመተግበሩ በፊት የክልሉ ከፍተኛ ኀላፊዎች ሊሠሩ የታሰቡ ግቦችን አውቀው እና ለይተው ወደ ተግባር እንዲገቡ ለማስቻል ሥልጠናው ማስፈለጉን ገልጸዋል፡፡
በሥልጣናው የሚሳተፉ አካላት ፖሊሲና እቅድ የሚያወጡ፣ በጀት የሚመሩ እና ዞንና ወረዳን የሚቆጣጠሩ በመኾናቸው በዕቅዱ መግባባት ላይ ተደርሶ እንዲተገበር ለማስቻል ያግዛል ነው ያሉት፡፡
እስካሁን በነበረው ልምድ የ25 ዓመታት ዕቅድ እንዳልነበርም አስታውሰዋል። የአጭር ጊዜ እና የመካከለኛ ጊዜ ዕቅዶች በረጅም ዘመን መዳረሻን የሚያመላክቱ አልነበሩም፤ ስለዚህ የረጅም ጊዜ ዕቅድ ማቀድ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
እንደ አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያና ቻይና ያሉ ያደጉ ሀገሮች ከ20 እስከ 25 ዓመታት ዕቅድ በማቀድ ለዜጎቻቸው ብልጽግናን ማምጣታቸውንም ተናግረዋል።
የረጅም ዘመን ዐቅድ ማቀድ ከረጅሙ ዘመን የመካከለኛ እና የአጭር ጊዜ እቅድ እያወጡ መተግበር አርቆ የማየት እድል ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡
ዛሬ የሚፈጸመው ሥራ ለዛሬ 25 ዓመት ምን ሊኾን እንደሚችል ገምቶ በረጅም ጊዜ ግብ ለመጣል ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
ዳይሬክተሮቹ በእቅዱ ላይ ምንድን ነው የታሰበው ? የሚለውን አውቀው እና በረጅም ጊዜ ምን እንመራለን? የሚለውን በዕውቀት ላይ ተመስርተው እንዲሠሩ መግባባት ላይ መድረስ ክልሉን ረጅም ርቀት እንዲጓዝ እንደሚያደርገው አመላክተዋል።
ዘጋቢ፡ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን