
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 21/2012 ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በረኸት ወረዳ ከአፋርና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ሊሠራ እንደሚገባ ነዋሪዎች ጠይቀዋል፡፡
የአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በረኸት ወረዳ ከአፋር እና ከኦሮሚያ ክልሎች ጋር የሚያዋስኑት ብዙ ቀበሌዎች አሉት፡፡ በእነዚህ አዋሳኝ አካባቢዎች የሦስቱ ክልሎች ሕዝቦች በተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያው ጉዳዮች ይገናኛሉ፡፡ ማኅበረሰቡ ሰላም ወዳድ፣ ለዘመናት አብሮ የሚኖር እና አሁንም መኖርን የሚሻ ቢሆንም አልፎ አልፎ ለኅብረተሰቡ ግልጽ ባልሆኑ ምክንያቶች ግጭቶች እንደሚፈጠሩ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
አብመድ በሰሜን ሸዋ ዞን በረኸት ወረዳ ተገኝቶ ካነጋገራቸው ነዋሪዎች መካከል አቶ ግርማ ክንፈ በአፋር እና አማራ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በሚኖሩ አርብቶ አደሮች እና አርሶ አደሮች መካከል የፀጥታ ችግሮች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡ ከሁለቱም ክልሎች የተውጣጡ የሰላም ኮሚቴ አባላት በሠሩት ሥራ ደግሞ ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ እንዳደረገው ገልጸዋል፡፡ በዚህ ወቅት እርሳቸው ከአፋር ክልል ገበያ ተገበያይተው በሰላም እንደሚመለሱም ተናግረዋል፡፡ የግጦሽ ቦታ ለእንስሶቻቸው በጋራ ይጠቀማሉ፤ ብዙ የበረኸት ወጣቶች ደግሞ ወደ አፋር ክልል በመግባት የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
የበረኸት ወረዳ ከሌሎች አካባቢዎች የተሻለ ሰላም እንዳለው አስተያየት ሰጪው ተናግረዋል፡፡ “ይህ ደግሞ የሰላም ዘብ የሆኑ የሰላም ኮሚቴ አባቶች ጠንክረው በመሥራታቸው ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡ የተገኘው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ደግሞ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ሊጠናክር እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
ኅብረተሰቡን ሊያስተሳስሩ የሚችሉ መሠረተ ልማቶችን በአዋሳኝ አካባቢዎች ላይ መሥራት፣ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራን ማጠናከር እና የሁለቱ ክልል ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በየጊዜው ተገናኝተው መነጋገር እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
አቶ መርሻ ማሞ የበረኸት ወረዳ የሰላም ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት በአዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት ይፈጠር እንደነበር አስታውሰው ችግሩን ለመፍታት የሀገር ሽማግሌዎች ሚና የጎላ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች ባህል የሚያውቁ፣ ሲናገሩ የሚደመጡ ሽማግሌዎች ተመርጠው የሰላም ኮሚቴ ሆነው በመሥራታቸው አሁን ያለው ሰላም መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ መርሻ ገለጻ ይህ ሰላም እንዲመጣ የሰላም ኮሚቴ አባላቱ የተመቻቸ መንገድ እንኳን ሳይኖር ከሰባት ሰዓት በላይ በእግር ተጉዘዋል፤ ለሳምንታት ስንቅ ቋጥረው፣ ከአዋሳኝ አካባቢዎች ጋር ውለው አድረው ተነጋግረዋል፡፡ በዚህም ሰላም እንደመጣ ተናግረዋል፡፡ የተበደለ እንዲተው፣ የተዘረፈም ንብረት እንዲመለስ፣ አዋሳኝ አካባቢዎች በግጦሽ መሬትን በጋራ እንዲጠቀሙ፣ በገበያ እና በተለያዩ ማኅበራዊ መስተጋብሮች እንዲገናኙ ተደርጓል ብለዋል፡፡ በተሠራው ሥራም የቡድን ስርቆት፣ ዘረፋ እና ግድያ እንዲቆም መደረጉን አቶ መርሻ አስታውቀዋል፡፡
የሰላም ኮሚቴ አባላቱ በወረዳው በኩል ትኩረት ባለመሰጠቱ ግንኙነት በመቋረጡ ግጭቶቹ እንዳያገረሹ የኅብረተሰቡም የሀገር ሽማግሌዎቹም ስጋት ነው፡፡ የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል መንግሥት ከኮሚቴው ጋር መሥራት እንዳለበት አቶ መርሻ አስገንዝበዋል፡፡ “ሰላሙን ለማይፈልጉ አካላት መጠቀሚያ እንዳይሆንም ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” ነው ያሉት፡፡
የበረኸት ወረዳ የሰላም እና የሕዝብ ደኅንነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወንድወሰን ሰይፈ “በረኸት ወረዳ አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ከሰላም ኮሚቴ (የሀገር ሽማግሌዎች) ጋር በተሠራው ሥራ የመጣው አስተማማኝ ሰላም ማኅበረሰቡ ያለስጋት እንዲኖር አስችሏል” ብለዋል፡፡ የሰላም እና ደኅንነት ጽሕፈት ቤት ደግሞ አሁን የተገኘው ሰላም እንዲመጣ የሰላም ኮሚቴ በማዋቀር እና ድጋፍ በማድረግ ሰፊ ሥራ መሥራቱን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በውጤቱም በቡድን መዝረፍ ቆሟል፣ በውኃ፣ በግጦሽ መሬት እና በሌሎችም ችግሮች ሰበብ ግጭት እየተነሳ የሰው ሕይወት ሲጠፋ የነበረውን ችግር በውይይት መፍታት ተችሏል ብለዋል፡፡
የኅብረተሰቡን መስተጋብር ለማጠናከር በአዋሳኝ አካባቢዎች የጋራ መስኖ ፕሮጀክት፣ የጋራ መንገድ ከመተህ ብላ እስከ አዋሽ እየተሠራ መሆኑን ኃላፊው ጠቅሰዋል፡፡
አሁን ላይ የጋራ ግጦሽ ስለሚጠቀሙ ተቀላቅለው የሚሄዱ ከብቶች ያለመመለስ እና ጥቃቅን ችግሮች እንደሚስተዋሉም ተናግረዋል፡፡ ቀድሞ ለመከላከል ከዚህ በፊት ሰላም እንዲመጣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተውን የሰላም ኮሚቴ ማጠናከረ እንደሚያስፈልግም በዕቅድ ይዘው እየሠሩ እንደሚገኙ አቶ ወንድወሰን አረጋግጠዋል፡፡ የሰላም ኮሚቴው እንደ ከዚህ በፊቱ በየጊዜው እየተገናኘ እንዳይ ሠራ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንቅፋት መፍጠሩንም አስረድተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው- ከበረኸት
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
