
ደብረ ማርቆስ: ሰኔ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛው እና በኤክስቴንሽን መርሐ ግብር በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና በሦስተኛ ዲግሪ ያስተማራቸውን ከ2 ሺህ በላይ ተማሪዎች አስመርቋል።
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሳይህ ካሰው (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራውን ከጀመረበት ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ የተማረ የሰው ኀይል በማፍራት ለሀገር ማበርከቱን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በምርምር እና በማኅበረሰብ አገልግሎትም እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ምሳሌ የሚኾን ነው ብለዋል።
ተመራቂ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀት በመጠቀም ለራሳቸው፣ ለወገናቸው እና ለሀገራቸው መልካም ተግባር ሊሠሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሥራውን በቴክኖሎጂ ለማስደገፍም እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ እና የዩኒቨርሲቲው የሥራ አመራር ቦርድ አባል ተሾመ ዋለ በየጊዜው የሚያጋጥሙ የሰው ልጅ ፈተናዎች በምርምር እና በቴክኖሎጂ የሚፈቱ መኾናቸውን ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲ ቆይታችሁ ያገኛችሁትን ዕውቀት እና ክህሎት በመጠቀም የኅብረተሰቡን ችግር የምትፈቱ ዜጎች ልትኾኑ ይገባል ነው ያሉት።
ተመራቂ ተማሪዎችም በብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አልፈው ለዚህ ስኬት በመብቃታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል። በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር ራሳቸውን እና ሀገራቸውን ለማገልገል በትጋት እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው በካሄደው 18ኛው ዙር የተማሪዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን