10ኛው የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

18

አዲስ አበባ: ሰኔ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድው 10ኛው የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር ኮንፈረንስ ወይም የአፍሪካ የሲቪል ሰርቪስ ቀን በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

በኮንፈረንሱ መልዕክት ያስተላለፉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ጠንካራ እና ከወቅቱ ጋር የዘመነ የሲቪል ሰርቪስ ሥርዓት መገንባት በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን መተማመን ያጠናክራል ብለዋል።

አሁን ላይ የመንግሥት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት በብዙ መልኩ እየተፈተኑ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቴክኖሎጂ፣ ሰላም እና ጸጥታ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ወረርሽኞች እና ሌሎች ተግዳሮቶች ዘርፉን እንደፈተኑት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እነዚህን ተግዳሮቶች መቋቋም የሚያስችል እና የሕዝቦቿን የልማት ፍላጎት እና ብልጽግና ማሳካት የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሠራች ነው ብለዋል። ለዚህም በቅርቡ አገልግሎት መስጠት የጀመረውን የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በማሳያነት አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ይህን ተሞክሮዋን ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም በማጋራት ከሌሎች ወንድም እና እህት የአፍሪካ ሀገራት በመማር የአህጉሩን የ2063 አጀንዳ ለማሳካት በወንድማማችነት ትብብር አብራ እንደምትሠራም አስታውቀዋል።

የኢፌዴሪ ሲቪል ሰርቨስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኀይሌ (ዶ.ር) በአፍሪካ የተከማቹ የአገልግሎት አቅርቦት ችግሮችን በመፍታት አካታች እና ዘላቂ ልማት የሚያመጣ ጠንካራ ተቋም አስፈላጊ መኾኑን ገልጸዋል።

አፍሪካ የተከማቹ ችግሮቿን ለመፍታትና የመጪውን ጊዜ ያለመ ተልዕኮ ለመፈጸም ጠንካራ የሰው ሀብት እና የመንግሥት አሥተዳደር የሚያስፈልጋት በመኾኑ መወያየት እና ተሞክሮ መቀያየር የኮንፈረንሱ ዓላማ መኾኑን ጠቅሰዋል።

ለሦሥት ቀናት በሚቆየው 10ኛው የአፍሪካ የሲቪል ሰርቪስ ቀን የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የሥራ ኀላፊዎች እና ዓለማቀፍ ተቋማት ኀላፊዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ:- ኢብራሂም ሙሃመድ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article‎ከቀጣዩ ወር ጀምሮ ግብርን በዲጂታል ዘዴ እንደሚሰበስብ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከጤና ባለሙያዎች ጋር ተወያዩ።