
ጎንደር: ሰኔ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ የዲጂታላይዜሽን ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል።ግብርን በዲጂታላይዜሽን መንገድ መሠብሠቡ የተገልጋዩን ጊዜ፣ ገንዘብ እና ጉልበት ለመቆጠብ እንደሚረዳ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ ኀላፊ ጥሩዬ አትክልት ተናግረዋል።
ዲጂታል የገቢ አሰባሰብ የአገልጋዩን ግልጸኝነት የሚጨምር በመኾኑ ለባለሙያዎች ሥልጠና ከመስጠት ጀምሮ አስፈላጊ ግብዓትን በማሟላት የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።በከተማዋ ከ14 ሺህ በላይ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ሲኖሩ ከሐምሌ 1/2017 ዓ.ም ጀምሮ ዲጂታል የገቢ አሰባሰብ ሥራ እንደሚጀመር ተገልጿል።
የገቢ አሰባሰቡ ባለመዘመኑ ምክንያት ከተማዋ ማግኘት የሚገባትን ገቢ ሳታገኝ ቆይታለች ያሉት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የጎንደር ከተማ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ግርማይ ልጅዓለም ከተማዋን ለማልማት ከሚያስፈልገው አቅም እና ፍላጎት አኳያ በርካታ መሠራት ያለባቸው ተግባራት መኖራቸውን ገልጸዋል። አሁንም የተጀመረው በዲጂታል ዘዴ ገቢን የመሰብሰብ ሂደት የተሻለ እንድንፈጽም ያግዛልም ብለዋል።
በዲጂታል ዘዴ ገቢን ለመሰብሰብ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማከናወናቸውን ያነሱት የማራኪ ክፍለ ከተማ ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ካሳሁን መኮንን የገቢ አሰባሰብ ሂደቱ መዘመን መልካም እድልን ይዞ ይመጣል ብለዋል።ተግባሩ መጀመሩ በግብር ከፋዮች በኩል የሚነሱ ብልሹ አሠራሮችን በማስቀረት ጉልበትን የሚቆጥብ መኾኑን የአዘዞ ጠዳ ክፍለ ከተማ ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ደስታው ሙሉነህ አስታውቀዋል።
ዘጋቢ:- ዳንኤል ወርቄ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን