ወልድያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስመረቀ።

13

ወልድያ: ሰኔ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ወልድያ ዩኒቨርሲቲ ለ12ኛ ዙር ተማሪዎችን አስመርቋል። የወልድያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አበበ ግርማ (ዶ.ር) ተመራቂ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ከመማር ማስተማር ባሻገር ኀረብረተሰባዊ ቁርኝት ያዳበሩበት ወቅት መኾኑን ገልጸዋል።

ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው ያካበቱትን ሁለንተናዊ ሀብት ለማኅበረሰብ ልማት እና ለሀገር ብልጽግና እንዲጠቀሙበትም አሳስበዋል። የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ እና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ አባል ዱባለ አብራሬ መማር ማለት ማመዛዘን እና ማሰላሰል መቻል መኾኑን ገልጸዋል። ተመራቂዎች ሚዛናዊ ትውልድ ኾናችሁ ሚዛናዊ ማኅበረሰብ የመገንባት ኀላፊነታችሁን ልትወጡ ይገባል ነው ያሉት።

በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የወልድያ ከተማ እና አጠቃላይ የሰሜን ወሎ ዞን ሕዝብን ጥልቅ ማንነት ተረድታችሁ የኅብረተሰቡ አካል ኾናችኋል ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ተመራቂዎች በሚሄዱበት አካባቢ ሁሉ የወልድያ፣ አካባቢዋ እና የዩኒቨርሲቲው አምባሳደር እንዲኾኑ አደራ ብለዋል።

በተለይም የወልድያ ከተማ እና ሕዝቦቿ የፍቅር ልጆቿ ኾናችሁ ለዛሬ ክብር በቅታችኋል፤ ወደፊትም በሥራ፣ በንግድ ወይም በኢንቨስትመንት ተመልሳችሁ በመምጣት በፍቅር ለክብር ካበቃችሁ ማኅበረሰብ ጋር እንድትሠሩ እጠይቃለሁ ነው ያሉት።

ወልድያ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በቀን እና በማታ መርሐ ግብር ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ 983 ተማሪዎችን ነው ያስመረቀው። አሚኮ ያነጋገራቸው የማእረግ ተመራቂ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ የሸመቱትን ዕውቀት መሬት ላይ በማውረድ ኅብረተሰቡን እንደሚያገለግሉ ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleጥናት እና ምርምሮች ወደ ተግባር ተቀይረው ችግር ፈቺ እንዲኾኑ እየተሠራ ነው።
Next article‎ከቀጣዩ ወር ጀምሮ ግብርን በዲጂታል ዘዴ እንደሚሰበስብ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ።