
ከሚሴ: ሰኔ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የከሚሴ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ 14ኛ የጥናት እና ምርምር ሲምፖዚዬም በከሚሴ ከተማ አካሂዷል።በሲምፖዚየሙ የኮሌጁ ጥናት ተመራማሪዎችን ጨምሮ የወረዳዎች እና የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በሲምፖዚየሙ ጥናት እና ምርምራቸውን ያቀረቡ መምህራን በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ባሉ ትምህርት ቤቶች ያለውን የትምህርት ጥራት ለማሻሻል በተመረጡ ትምህርት ቤቶች ጥናት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የከሚሴ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ዲን ተፈሪ መኮንን ኮሌጁ ከተሰጠው ኀላፊነቶች ውስጥ ችግር ፈቺ ምርምሮችን ለማኅበረሰቡ ማቅረብ መኾኑን ጠቅሰዋል። 22 የሚኾኑ ምርምሮችን በማዘጋጀት ለሚመለከታቸው አካላት እያቀረበ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የሚሠሩ ምርምሮችን ወደ ተግባር በመቀየር በትምህርት ቤቶች የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ከዚህ ቀደም ውስንነቶች መኖራቸውን ገልጸዋል። አሁን ላይ ግን የሚሠሩ ጥናት እና ምርምሮች ወደ ተግባር ተቀይረው ችግር ፈቺ እንዲኾኑ ከወረዳ እና ከተማ አሥተዳደሮች ጋር በጋራ እየሠራን ነው ብለዋል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የሚቀርቡ የጥናትና ምርምር ዳኛ መምህር ሙሉጌታ ጓንጉል የወሎ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰቡን ችግር ለመቅረፍ ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማዘጋጀት ከአሥተዳደር መዋቅሮች ጋር በቅርበት እንደሚሠራ አብራርተዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ እንድሪስ አህመድ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ በትምህርት ዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስተካከል ከወሎ ዩኒቨርሲቲ እና ከኮሌጁ ጋር በመኾን እየሠሩ መኾኑን አስረድተዋል። በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ያለውን የትምህርት ተደራሽነት ሽፋን ለማሳደግ ማኅበረሰቡን ያሳተፈ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሒም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን