“አርቆ ማየት እና አልሞ መሥራት ለሕዝባችን ከፍታ አስፈላጊ ነው” አቶ አረጋ ከበደ

21

ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “አርቆ ማየት አልሞ መሥራት” በሚል መልዕክት በአማራ ክልል የተቋማት ዳይሬክተሮች የአሻጋሪ ዕድገት እና ዘላቂ ልማት ዕቅድ ዙሪያ ሥልጠና በባሕር ዳር ከተማ ዛሬ ተጀምሯል።
በመድረኩ መክፈቻ ላይ የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ፣ የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ እና ሌሎችም የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ ሥልጠናው ትኩረት የሚያደርገው በ2018 በጀት ዓመት ወደ ተግባር የሚገባው የአምስት ዓመት ዕቅድ እና የ25 ዓመት ፍኖተ ካርታ ውይይት መኾኑን አንስተዋል። እቅዱ ለተሳታፊዎች የሚቀርብ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

የተፈጥሮ ጸጋዎቻችንን ለክልላችን የችግር መፍቻ እና ከድህነት መውጫ አድርገን ልንጠቀምበት ይገባል ነው ያሉት፡፡ ይህ መድረክ ለጋራ ራዕይ እና የጋራ አመራር የሚረጋገጥበት እና ሕዝባችን የኖረበትን የድህነት አዙሪት ለማላቀቅ ቃል ኪዳን የምንገባበት ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይ የሥልጠና ቀናት ከመድረኩ የሚገኙ ሃሳቦች የክልሉን ችግሮች እና መንስኤዎች በጥልቀት በመመርመር የመፍትሄ ሃሳቦችን ይዞ በቀረበው ፍኖተ ካርታ ላይ በመወያየት ለላቀ ትግበራ የምንዘጋጅበት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ዕቅዱ ዓለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ የደረገ መኾኑን አንስተው የውይይት ሰነዱ የማክሮ ኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ እድገቶችን የሚተነትን እና ግቦችንም የሚያስቀምጥ ስለመኾኑም ገልጸዋል፡፡

ሠልጣኞች ከሥልጠና በኋላ የሚጠበቁባቸውን ነጥቦችም አንስተዋል፡፡ ለአብነትም በዕቅዱ ላይ የጋራ ፍላጎት እና ራዕይ፣ ክልላዊ እና ተቋማዊ ግቦችን ለማሳካት በአንድ ትውልድ የሚፈጸም ባለመኾኑ ተቀብሎ ለማቀበል የሚያስችል ዝግጅት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ርእሰ መሥተዳድሩ አስረው ከያዙን የአመራር፣ የተቋም እና የማኅበረሰብ አጉል ልማዶች በመላቀቅ ባለንበት ሁኔታ እሴት ለመጨመር መትጋት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ክልላችን በግጭት ውስጥ የቆየ እና ከድህነት ጋር ተዳምሮ ያለውን የማኅበረሰባችን ችግር ለማላቀቅ የሚያስችል ሥራ ለመሥራት የተዘጋጀ ዕቅድ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም ፍኖተ ካርታውን እና ዕቅዱን ተገንዝቦ ባለቤት በመኾን የሚጠበቁ ቁልፍ ሚናዎች የሏቸውን አንስተዋል፡፡ ከነዚህም መካከል በእቅዱ ላይ ጥልቅ የኾነ ግንዛቤ ሊኖር ይገባል፡፡ ስትራቴጂያዊ አመራርን ማረጋገጥ እና ለታችኛው መዋቅር ከዞን እስከ ቀበሌ ድረስ እንዲሁም ለሕዝቡ በተገቢው መንገድ ማስረዳት እና ማሳተፍ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡ ስለኾነም አመራሩ አርቆ ማየት እና አልሞ መሥራት ለሕዝባችን ከፍታ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ፍሬሕይዎት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“መሶብ ውጤታማ፣ አካታች፣ ልዩ እና ተወዳዳሪ አገልግሎቶችን የማቅረብ ቃልኪዳን ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleጥናት እና ምርምሮች ወደ ተግባር ተቀይረው ችግር ፈቺ እንዲኾኑ እየተሠራ ነው።