“መሶብ ውጤታማ፣ አካታች፣ ልዩ እና ተወዳዳሪ አገልግሎቶችን የማቅረብ ቃልኪዳን ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

14

ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የአፍሪካ የሲቪል ሰርቪስ ቀን በዓልን እና የተመድ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ጉዳዮች ጉባኤን አስጀምረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት መሶብ የአንድ ማዕከል ሥራችን ለሰው ተኮር አገልግሎት አቅርቦት መሳለጥ የገባነውን ቃል ኪዳን መሳካት መገለጫ ነው ብለዋል። ዛሬ የአፍሪካ የሲቪል ሰርቪስ ቀን በዓልን እና የተመድ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ጉዳዮች ጉባኤን አስጀምረናል ነው ያሉት።

መሶብ ውጤታማ፣ አካታች፣ ልዩ እና ተወዳዳሪ አገልግሎቶችን የማቅረብ ቃልኪዳን ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገልግሎት አሰጣጥ ማንም ወደኋላ እንዳይቀር ከሕዝብ ጋር የተገባ የኪዳን ቃል ማሳያ ነው ብለዋል። ባለፉት የለውጥ ዓመታት ታሪካዊ ጉድለቶችን እና ክፍተቶችን እየሞላን፣ የሕዝብ አገልግሎቶችን ወደ ሁሉም የሀገራችን ማዕዘናት እያዳረስን እንገኛለን ነው ያሉት።

በሰባት ምሥሥዎች ላይ በተመሰረተው የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርማችን፤ አዲስ እና ልዩ ተቋማዊ መዋቅር እየገነባን፣ የሰው ሃብት አሥተዳደርን እያዘመንን እና ዲጂታላይዜሽን እያፋጠንን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአገልግሎት አሰጣጥ ማዕቀፍን ተግባራዊነት የምናረጋግጥበት ነው።

በተጨባጭ ራዕይ እና በትጋት መሥራታችን ውጤት እያስመዘገበ ነው። ዜጎቻችን በክብር እየተስተናገዱ፣ መሰናክሎችን እየቀነስን እንገኛለን ነው ያሉት። በጉባኤው ኢትዮጵያ ልምዷን እንደምታካፍልም ገልጸዋል። ከሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞቻችንም ትማራለች ነው ያሉት። ይህን ጉባኤ በልዩ ጥረት ላሰናዳችሁ አካላት ልባዊ ምስጋናዬን ለማቅረብ እወዳለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የማኅበረሰብ ደኅንነት አጠባበቅ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
Next article“አርቆ ማየት እና አልሞ መሥራት ለሕዝባችን ከፍታ አስፈላጊ ነው” አቶ አረጋ ከበደ