
‘‘ወለህ ላይ የሚሠራው የቃሰና ወንዝ ጠለፋ ሚያዝያ 30 ይጠናቀቃል፡፡’’ የተቋራጩ አውሥኮድ የፕሮጀክቱ መሐንዲስ
‘‘የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 80 በመቶ ሳይሆን 25 በመቶ ነው፡፡’’ የአማራ ዲዛይንና ቁጥጥር ሥራዎች ድርጅት መሐንዲስ
‘‘የከተማዋን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከጥናት ባሻገር በዕቅድ የተያዘ የፕሮጀክት ሐሳብ የለም፡፡’’ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 21/2012 ዓ.ም (አብመድ) በየዓመቱ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ጥም ጥያቄ የተለመደ ነው፡፡ በዓመት ውስጥ 10 ወራትን የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር እንዲፈታ ይጠይቃሉ፤ ገሚሱ ደግሞ ‘‘በ20 ቀናት አንድ ጊዜ የሚደርሰው ወረፋ በስህተት አልፎናል’’ በሚል ስሞታ በከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ጽሕፈት ቤቶች በር አይጠፋም፡፡
ከምንም በላይ ውኃ ተራው በምን ሰዓት እንደሚለቀቅ ባለመታወቁም በቧንቧ አፍ ሥር ዓይንን ሳይነቅሉ ቀን ከሌሊት መጠበቅ እንዳማረራቸው የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ አድና ተማረ ለአብመድ ተናግረዋል፡፡ በጋራ የውኃ ቦኖዎች ልጃቸውን አዝለው የተገኙት ወይዘሮ አድና የንጹሕ መጠጥ ውኃ እጥረት ባለፉት 10 ዓመታት እንደተባባሰና በየዓመቱ ለመንግሥትና ለመገናኛ ብዙኃን ቢናገሩም ምላሽ ማጣታቸውን ገልጸዋል፡፡
‘‘አንድ ጀሪካን ውኃ እስከ 10 ብር የመግዛት አቅም የለንም’’ ያሉት ወይዘሮ አድና ቀኑን ሙሉ ልጅ አዝለው የውኃ ተራ በመጠበቅ ጊዜና ጉልበታቸውን እያባከኑ እንደሚኖሩ ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ አድና የውኃ እጥረቱ ለእናቶችና ሕጻናት የከፋ ጉዳት ሲኖረው የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ደግሞ ተገቢውን አገልግሎት እንዳይሰጡ ማድረጉን ገልጸዋል፤ የከተማዋን ሁለንተናዊ ዕድገት እየተፈታተነ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ሌላዋ የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር 01 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ወርቅ አሰፋ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ ሴቶች ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ውኃ ለመቅዳት ብቻ በማዋላቸው ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን መመለስ እንዳይችሉ እያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
‘‘መንግሥት ክረምት ባለፈ ቁጥር በየዓመቱ ‘የከርሰ ምድር ውኃ እጥረት አለ’ እና ‘ዕቃ ተሰበረ’ በማለት ጥያቄያቸውን መመለስ እንዳልቻለ ወይዘሮ ወርቅ ገልጸዋል፡፡
የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ውኃና ፈሳሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኃላፊ አቶ ሰሎሞን መለሰ ‘‘በከተማዋ መሠረታዊ የውኃ እጥረት አለ’’ ብለዋል፡፡ በዝናብ እጥረት ምክንያት የከርሰ ምድር የውኃ ምንጮች መጠን በግማሽና ከዚያ በላይ ቀንሰዋል፡፡ በከተማዋ ከ41 ሺህ በላይ ሕዝብ እንዳለ የተናገሩት አቶ ሰሎሞን ‘‘ለሕዝቡ በየቀኑ 50 ሊትር ውኃ በሰከንድ ማቅረብ ያስፈልጋል፤ አሁን ከተማዋ የምታገኘው ግን 15 ሊትር በሰከንድ ብቻ ነው’’ ብለዋል፡፡ በዚህ ምክንያት የከተማዋ ነዋሪ በየ15 ቀኑ እና በየ20 ቀኑ ውኃ እንዲቀዳ መገደዱን አስታውቀዋል፡፡
ችግሩ ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ከበርካታ ዓመታት በፊት ለክልሉ መንግሥት ማስታወቃቸውንም ተናግረዋል፡፡ ችግሩን ለመቀነስ ክልሉ አስቸኳይ ፕሮጀክት ወለህ ቃሰና ወንዝ ጠለፋን ለአውስኮድ በ2011 ዓ.ም በ10 ወራት እንዲጠናቀቅ ቢሰጥም ሥራው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እንዳልቻለ አስታውቀዋል፡፡ ለከተማዋ የረጅም ጊዜ የውኃ አማራጭ መፍትሔ በ2009 ዓ.ም በወቅቱ የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ገዱ አንዳርጋቸው የሽላሽማን አፈር ግድብ እንዲሠራ ቃል ቢገባም እስከዛሬ ተግባራዊ እንዳልተደረገ አስታውቀዋል፡፡
የአማራ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት የሳይት መሐንዲስ ዑመር አወል ከአብመድ ጋር በነበራቸው ቆይታ ‘‘ወለህ ላይ የሚሠራው የቃሰና ወንዝ ጠለፋ ሚያዝያ 30 ይጠናቀቃል’’ ብለው ከወር በፊት ቢናገሩም እስከ ግንቦት 21 ቀን 2012ዓ.ም ድረስ ሥራው በጅምር ነው፡፡ ‘‘በ46 ሚሊዮን ብር የሚሠራው የቃሰና የወንዝ ጠለፋ 18 ሊትር ውኃ በሰከንድ ያመርታል’’ ያሉት አቶ ዑመር ፕሮጀክቶች አንዳንድ ጊዜ ሊዘገዩ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ የቃሰና ወንዝ ጠለፋ ፕሮጀክትም ዛሬ ላይ ገና 80 በመቶ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአማራ ዲዛይንና ቁጥጥር ሥራዎች ድርጅት የቃሰና ወንዝ ጠለፋ ፕሮጀክት አማካሪ ኢንጂነር ቢሆነኝ ዓድማሱ ደግሞ ‘‘የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 80 በመቶ ሳይሆን 25 በመቶ ነው’’ ብለዋል፡፡ ‘‘የሰቆጣ ከተማን አስቸኳይ የውኃ ፍላጎት ለመመለስ በ2011 ዓ.ም በ10 ወራት ለማጠናቀቅ ወደሥራ የገባ ፕሮጀክት ቢሆንም አፈጻጸሙ በ2012 ዓ.ም የማለቅ ዕድል የለውም’’ ነው ያሉት፡፡ የውኃ ፕሮጀክቱ የዘገየበትን ምክንያት ሲገልጹም ‘‘ሲስተም የሚያገናኙ ግዥዎች ባለመፈጸማቸው፣ በቂ ቁሳቁስና ባለሙያ ባለመኖሩ ነው’’ ብለዋል፡፡
ይህ የውኃ ፕሮጀክት ቢጠናቀቅ እንኳ ለሰቆጣ ከተማ አስተዳደር የውኃ እጥረት ‘‘ዘላቂ መፍትሔ አይደለም’’ ያሉት ኢንጂነሩ የዝናብ እጥረት ባለበት አካባቢ የደረቁ ወንዞችን ገድቦ መፍትሔ ማድረግ እንደማይቻል ነው ያመለከቱት፡፡ ኢንጂነር ቢሆነኝ እንደተናገሩት ለሰቆጣ የውኃ አቅርቦት ችግር የአጭር ጊዜ መፍትሔው በወንዞች አካባቢ ያሉ ባሕር ዛፎችን በመንቀል ውኃን የሚጨምሩ ዛፎችን መትከል፣ የአካባቢውን የተፈጥሮ ሀብት ማልማት ነው፤ በረጅም ጊዜ ደግሞ ከትልልቅ ወንዞች ውኃ መጥለፍ የተሻለ ነው፡፡
የአማራ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት (አውሥኮድ) የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ ብርሃኑ ዮሐንስ የቃሰና ወንዝ ጠለፋ ፕሮጀክት መጓተት የተፈጠረው የውኃ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ በወቅቱ በጀት ባለመልቀቁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ጥሬ ዕቃዎች በገበያ ላይ ያለመገኘትም ሥራውን ማጓተቱን አቶ ብርሃኑ ጠቅሰዋል፡፡ በቅርቡ አስፈላጊ ጥሬ ዕቃዎች እየተሟሉ ቢሆንም የበጀቱ አለመለቀቅ ግን ሥራው ቶሎ እንዳይጠናቀቅ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አደም ወርቁ በበኩላቸው ‘‘ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ በቢው የበጀት እጥረት ተከስቷል’’ ብለዋል፡፡ ‘‘ፕሮጀክቱን ለማስቀጠል ሌላ በጀት ያስፈልገዋል’’ ያሉት ዳይሬክተሩ ቢጠናቀቅም የሰቆጣ ከተማ አስተዳደርን የውኃ ፍላጎት ‘‘በዘላቂነት አይፈታውም’’ ነው ያሉት፡፡
አቶ አደም እንደተናገሩት የሰቆጣን የውኃ እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት በርካታ ጥናቶች ቢካሄዱም የከርሰ ምድር ውኃ እጥረት መኖርና የሚገኙትም ውስን ውኃ ብቻ ማመንጨታቸው እስካሁን የሕዝቡ ጥያቄ እንዳይመለስ አድርጓል፡፡
በቢሮው የከተማዋን የንጹሕ መጠጥ ውኃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከጥናት ባሻገር በዕቅድ የተያዘ የፕሮጀክት ሐሳብ እንደሌላም አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
