የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የማኅበረሰብ ደኅንነት አጠባበቅ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

9

ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ እንደገለጹት በክልሉ ባለፉት ዓመታት የማኅበረሰቡን ደኅንነት የሚጎዱ ችግሮች መከሰታቸውን ገልጸዋል።

በተለይም ደግሞ በሰሜኑ ጦርነት እና ባለፉት ዓመታት ደግሞ በክልሉ ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ ለችግሩ እንደ አንድ አባባሽ ምክንያት ተደርጎ እንደሚወሰድ ገልጸዋል። የችግሩ አሳሳቢነት በጥናት መታገዙ ደግሞ የጥናቶችን ስፋት ተረድቶ መፍትሄ ለመስጠት ያግዛል ብለዋል።

በጥናት የተገኙ ውጤቶችን ተቋማት በእቅድ በማካተት የማኅበረሰቡን ደኅንነት ማስጠበቅ ይገባል ብለዋል። አሁን የሚታየውን የሰላም መሻሻል ወደ ዘላቂ ሰላም በማምጣት የሁሉም ድርሻ ሊኾን ይገባልም ብለዋል። የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በላይ በዛብህ እንዳሉት ኢንስቲትዩቱ ከሚሠራቸው ሥራዎች ጤና እና ጤና ነክ በኾኑ ጉዳዮች ላይ ምርምሮችን ማድረግ አንዱ ነው።

በዚህም በሰሜኑ ጦርነት በክልሉ የጤናው ዘርፍ ላይ የደረሰውን ጉዳት ጥናት ተደርጎ ተቀባይነት ባላቸው ዓለም አቀፍ መጽሔቶች ጭምር እንዲታተም ተደርጓል ብለዋል። በዚህም በክልሉ የደረሰውን የጉዳት መጠን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጭምር እንዲያውቀው እና ረጅ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ድጋፍ እንዲያደርጉ ተደርጓል ብለዋል። አሁን ላይም በክልሉ ራስን በማጥፋት፣ በእገታ፣ በጠለፋ እና በንብረት ዝርፊያ ላይ ጥናቶችን ማካሄዱን ገልጸዋል። ችግሩን ለመቅረፍ ተቋማት ትኩረት ሠጥተው እንዲሠሩ ጠይቀዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሰራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article“ሀገሪቱ ከችግር ውስጥ የምትወጣው የተማረው ዜጋ በአመክንዮ ማሰብ ሲጀምር ነው” ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ.ር)
Next article“መሶብ ውጤታማ፣ አካታች፣ ልዩ እና ተወዳዳሪ አገልግሎቶችን የማቅረብ ቃልኪዳን ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ