
ባሕር ዳር: ሰኔ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች አስመርቋል። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ.ር) ትምህርት የማያቋርጥ ሂደት መኾኑን ገልጸዋል። የዕለቱ ተመራቂ ተማሪዎች ወደ አዲስ ምዕራፍ የምትሸጋገሩበት በመኾኑ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በስድስተኛው ዙር ምረቃ በመደበኛ እና በተከታይ የትምህርት ክፍል 3ሺህ 917 ተማሪዎችን በበመጀመሪያ ዲግሪ፣ 251 ተማሪዎችን በሁለተኛ ዲግሪ፣ በሥነ ማስተማር እና በከፍተኛ ዲፕሎማ 303 ተማሪዎችን በአጠቃላይ 4ሺህ 471 ተማሪዎችን በ48 የቅድመ ምረቃ እና በ28 የድህረ ምረቃ የትምህርት ክፍል በ76 የትምህርት ዓይነቶች አስመርቋል ነው ያሉት፡፡
ከእነዘህ ውስጥ 37 በመቶ የሚኾኑት ተመራዎች ሴቶች እንደኾኑም ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት አምስት ዙሮች 4ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን በማስመረቅ ለሀገር ዕድገት የራሱ አሻራ ማሳረፉን አብረርተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በ2017 ዓ.ም ካስፈተናቸው ሀገር አቀፍ የመውጫ ፈተና 92 ከመቶ ማለፋቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ይህ ውጤት ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ከፍሎችን ከማስፋፋት ባለፈ ለትምህርት ጥራት የሰጠው ትኩረት ከፍ ያለ መኾኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡ እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲ እንደመኾኑ መጠን የሚገኝበትን አካባቢ ጸጋ በመለየት ለሀገር በሚጠቅም አግባብ እየሠራ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ጸጋ በአራት ዘርፍ በመክፈል በግብርና፣ አረንጓዴ ልማት በኅብረተስብ ጤና፣ በቱሪዝም ልማት፣ በሀገር በቀል ዕውቀት እና በአገው ባሕል እና ቋንቋ ልማት ልቆ ለመውጣት የአምስት ዓመት ስትራቴጅ ልማት አቅዶ እየሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና የቴከልኖሎጅ ሽግግርን ለማሳለጥ በሰባት ኮሌጆች በሁለት ትምህርት ቤቶች እና በአንድ የአገው ጥናት ባሕል ማዕክል የተደራጀ ዩኒቨርሲቲ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የትምህረት ጥራትን ለማረጋገጥ መምህራንን በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር እያስተማረ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት፡፡
እንደ ሀገር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ዩኒቨርሲቲው በ50 የትምህርት ጥራት ኦዲት ፕሮግራም በማከናወን እንደሀገር ዕውቅና ለማግኘት ጥረት እየተደረገ መኾኑን አስረድተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው 10 የሁለተኛ ዲግሪ እና 3 የሦስተኛ ዲግሪ የትምህርት ክፍል ለመክፈት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ ከመማር ማስተማር በተጨማሪ የምርምር እና የቴክኖሎጅ ሽግግር ሥራ በመሥራት የዩኒቨርሲቲውን ተልዕኮ እየተወጣም ይገኛል ነው ያሉት።
ሰፊ የምርምር ሥራ ለመሥራት ዕቅድ ይዞ ሲንቀሳቀስ የቆየ ቢኾንም በተፈጠረው የሰላም እጦት ምክንያት የምርምር ሥራው ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች እንዲገደብ ማድረጉን ነው የተናገሩት፡፡ ዩኒቨርሲቲው በምርምር ያወጣቸው የምርምር ሥራዎች በዓለማቀፍ ጆርናሎች መውጣታቸውን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ይህም ዩኒቨርሲቲውን ዓለም ዓቀፍ ተቀባይነት እንዲኖረው እንደሚያግዝ ነው የጠቆሙት፡፡
በእንጅባራ እና አካባቢ ያሉ ትምህርት ቤቶችን በመደገፍ እና ሥልጠና በመስጠት ኀላፊነቱን መወጣቱን ገልጸዋል። ለአካባቢው በማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት መጸዳጃ ቤት እና መንገድ በመሠራት አካቢውን እያገዘ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል፡፡ ከ50 ሚሊዮን በላይ ብር ዩኒቨርሲቲው ወጭ አድርጎ የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጠቱንም ተናግረዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው በሀገር በቀል ዕውቀት እና በአገው ታሪክ ባሕል እና ቋንቋ ጥናት ላይ ለመሥራት የአገው ጥናት ኢንስቲቲዩትን በ2013 ዓ.ም አቋቁሞ ሲሠራ መቆየቱን ነው የተናገሩት፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለሰው እና ለእንሰሳት ለመድኃኒትነት የሚያገለግሉ ዕጽዋትን በግማሽ ሄክታር የማልማት ሥራ እየተሠራ እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡
የአገው ፈርስ በዓልን በዩኒስኮ ለማስመዝገብ ጥረት እያደረገም ይገኛል ነው ያሉት፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለመምህራን እና ለተማሪዎች ምቹ ለማድረግ አረንጋዴ ልማትን በመደበኛነት እየሠራ ስለመኾኑም ተናግረዋል፡፡
ለመምህራን ቤት እና ምቹ ኹኔታ የመፍጠር ሥራ መሥራቱን የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ከ9 ቢሊዮን በር በላይ ወጭ በማድረግ በግቢው ውስጥ የማስዋብ እና ልዩ ልዩ የግንባታ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም አስገንዝበዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በቴክኖሎጅ እንዲታገዝ ለማድረግ ሰፊ ሥራ ስለመሥራቱም ጠቁመዋል፡፡ ተመራቂ ተማሪዎች ለሕዝባቸው ችግርን የሚፈቱ እንዲኾኑ እና ለሕዝብ በመቆርቆር እንዲሠሩም ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል፡፡
ሀገሪቱ ከችግር ውስጥ የምትወጣው የተማረው ዜጋ በአመክንዮ ማሰብ ሲጀምር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህን ታሳቢ አድርገው ለሀገራቸው እንዲሠሩም አሳስበዋል፡፡ ተመራቂ ተማሪዎች በየሄዱበት ሁሉ አምባሳደር በመኾን ዩኒቨርሲቲውን እንዲያስተዋውቁም አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን