
እንጅባራ: ሰኔ 14/2017 ዓ.ም (አሚኮ) እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች አስመርቋል። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)፣ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው፣ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጋርዳቸው ወርቁን (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኀላፊዎች፣ ተመራቂ ተማሪዎች እና የተማሪ ወላጆች ተገኝተዋል። ዩኒቨርሲቲው ለ6ኛ ዙር ነው ተማሪዎችን ያስመረቀው።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ተመራቂ ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጆች እና መምህራን እንኳን አደራሳችሁ፣ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በአጭር ጊዜ የአካባቢውን ሕዝብ እና የኢትዮጵያን የትምህርት ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ በርካታ ሥራዎችን መሥራቱን ገልጸዋል። የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ኢትዮጵያ ጉራማይሌ በኾኑ ክስተቶች በተወጠረችበት ጊዜ የሚካሄድ ታሪካዊ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ነው ያሉት ዶክተር ሙሉነሽ ደሴ የእናንተ መመረቅ ለኢትዮጵያ እና ለሕዝቦቿ ትልቅ ተስፋ እና ሐሴት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የትምህርት ፍላጎቷ እና ልምዷ ከሌሎች ቀደምት ሀገራት ቀድማ የምትገኝ መኾኗንም አንስተዋል። ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ በሃይማኖት ተቋማት የሃይማኖት አባቶች ድንጋይ ጠርበው፣ ብራና ፍቀው፣ ቀለም በጥብጠው ትምህርት የጀመሩባት ታሪካዊት እና ቀደምት ሀገር ናት ብለዋል።
በዘመናዊ የትምህርት ሥርዓትም ከአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ትምህርትን በሥርዓቱ ለማስሄድ ጥረት ያደረገች ሀገር ናት ነው ያሉት። ጥያቄ የሚኾነው ትምህርትን ከማንም ቀድመን የጀመርን ኾኖ ሳለ የጥራት ብቻ ሳይኾን የተሳትፎ ችግሮች አብረውን መዝለቃቸው ነው ብለዋል። ይህም መፍትሔ የሚሻ እና የእኔን እና የእናንተን የመማር ትርጉም የሚጠይቅ ነው ይላሉ።
የዓለም ታሪክ እና አሁናዊ ሁኔታ የሚያሳየው ያደጉ ሀገራት ለትምህርት ተሳትፎ፣ ተደራሽነት፣ ጥራት እና ፍትሐዊነት ትኩረት በመስጠታቸው ነው ብለዋል። ይህንን ያላደረጉ ደግሞ የብጥብጥ እና ግጭት፣ የሰላም እና ፍትሕ ጉድለት፣ ድህነት እና ኋላቀርነት ላይ ወድቀዋል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ መንግሥት የነበሩ ችግሮችን ለቅሞ በማውጣት፣ የኢትዮጵያን ሰላም እና ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ጥረት እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል። “የነገ ሀገር የምትመስለው የዛሬ ተማሪዎችን ነው” ያሉት ኀላፊዋ የትምህርት ጥራቱ ተጠብቆ፣ ተወዳዳሪ የኾኑ፣ በሳይንሳዊ እውቀት የተቀኙ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂን የሚፈጥሩ፣ የተፈጠሩትን የሚጠቀሙ፣ የረቀቀ አስተሳሰብ ያላቸው፣ ሀገራቸውን እና ወገናቸውን የሚወዱ ወጣቶችን ማፍራት ከተቻለ ሀገር ትለማለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ የምትጠብቀውም ይሄን መኾኑን ነው የተናገሩት። ትምህርት የእውቀት መሸጋገሪያ እና የፍትሐዊ ሃብት ክፍፍል ማረጋገጫ ነው ብለዋል። ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል የሚረጋገጠው ዘመኑ የሚዋጀውን እውቀት እና ክህሎት፣ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂን መጠቀም ሲቻል መኾኑን ነው የተናገሩት።
ቴክኖሎጂ የሰውን ጉልበት ከመተካት አልፎ የሰውን አስተሳሰብን በመተካት በሚገኝበት ዘመን ላይ ነን ያሉት ኀላፊዋ ትውልዱ ወሳኝ የትምህርት መስኮች ላይ መወዳደር ካልቻለ፣ ሥራ ማግኘት እና መኖር አዳጋች ነው ብለዋል።
የቴክኖሎጂ ዝግጁነትን ማረጋገጥ የሚቻለው በትምህርት እና በትምህርት ብቻ መኾኑንም ተናግረዋል። ትምህርት በዘመናዊ ማኅበረሰብ ውስጥ የቀጣዩን ትውልድ ይመራል ነው ያሉት። በምክንያት የሚያምን ትውልድ ለመቅረጽ የትምህርት ሥርዓቱ የማኅበረሰብ አምዶች ሳይሸራረፉ ማስቀጠል እንደሚገባ ነው ያመላከቱት።
መንግሥት ለትምህርት የሚበጅተው በጀት፣ ወላጆች ለትምህርት የሚያወጡት ወጪ ሲታይ ትምህርት ከምጣኔ ሃብት አንጻር ትልቅ ኢንዱስትሪ ነው ማለት ይቻላል ነው ያሉት። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተልዕኳቸው በእውቀት፣ በክህሎት፣ በአመለካከት እና በሥነ ምግባራቸው ብቁ የኾኑ ሥራ ፈጣሪ ምሩቃንን ማፍራት፣ ሀገራዊ እና የዓለማቀፋዊ ፋይዳ ያላቸው ጥናት እና ምርምሮችን በማካሄድ ለማኅበረሰቡ ሁለንተናዊ ብልጽግና እና አገልግሎት መሥጠት ነው ብለዋል።
ተልዕኳቸው የሚሳካው ዩኒቨርሲቲዎች ዙሪያቸው ሰላም ሰፍኖ ሁሉም የዩኒቨርሲቲው አካላት ፍጹም ሰላማዊ እና ከስጋት ነጻ ኾነው ተልዕኳቸው ላይ ማተኮር ሲችሉ ብቻ መኾኑን ነው የተናገሩት። የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ተልዕኮውን በመረዳት፣ የመማር ማስተማሩን ሰላማዊ በማድረግ ያሳካው ውጤት ለሌሎችም ምሳሌ የሚኾን ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከእናንተ ብዙ ትጠብቃለች ያሉት ኀላፊዋ ሁላችሁም ከመንግሥት እና ከሕዝብ ጎን በመቆም የኢትዮጵያን ዋነኛ ጠላት የኾነውን ድህነት ማጥፋት፣ ወደ ብልጽግና ለምናደርገው ጉዞ የበኩላችሁን እንድትወጡ አደራ እላለሁ ነው ያሉት። በተናጠል ትግል ብቻ የሚመዘገብ ሙሉ ስኬት እንደሌለም ተናግረዋል። የተባበረ ተሳትፎ የሀገርን ዕድገት እና ብልጽግና ለማረጋገጥ የማይተካ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።
በየተሰማሩበት የሙያ መስክ ሁሉ መከባበር፣ መደማመጥ፣ ታታሪነት እና ቅንነት በሞላበት ሥራ ኢትዮጵያን እንዲያሻግሩ ጠይቀዋል። በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ኀብረ ብሔራዊነትን፣ ሀገር ወዳድነትን እና የሀገር ፍቅርን እንደተማሩ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ኋላቀር ከኾኑ አመለካከቶች እንዲርቁም አሳስበዋል። ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ብቻ ሳትኾን የተፈጥሮም ምንጭ ናት ያሉት ኀላፊዋ ነጻነትን በራሷ አቅም አስከብራ ቅኝ ያልተገዛች፣ የዓድዋ ድል ባለቤት፣ ታላቅ ታሪክ ያለው ሕዝብ ያላት፣ በአፍሪካ ቀዳሚ የኾኑ በዩኒስኮ የተመዘገቡ የማይዳሰሱ እና የሚዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት፣ ኅብረ ብሔራዊት ሀገር ናት ብለዋል።
ባለጸጋ ኾና ሳለ ከበለጸጉ ሀገራት ተርታ እንዳትሰለፍ ያደረጓትን ምክንያቶች ለይተን፣ ከግጭት አዙሪት ወጥተን፣ የበለጸገች ሀገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ከጎን እንደምትሰለፉ እምነት አለኝ ነው ያሉት። የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ለሕግ የበላይነት፣ ለሀገር አንድነት፣ ለትምህርት እና ሥልጣኔ ቀና አመለካከት ባለው ማኅበረሰብ መካከል በመቋቋሙ በተመሠረተ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመማር ማስተማር፣ በምርምር እና በማኅበረሰብ አገልግሎት ብዙ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል። በምርምር እና በማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት እያደረገው ያለው ተግባር የሚደነቅ መኾኑንም ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው ለሚሠራው በጎ ተግባር ሁሉ የክልሉ መንግሥት ከጎኑ እንደሚቆምም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን