
ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ድጋፍ አሰባሳቢ እና አሥተባባሪ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድጋፋቸውን ላበረከቱ ግለሰቦች እና ተቋማት የምስጋና እና እውቅና መርሐ ግብር አካሂዷል።
ምስጋና እና እውቅና ካገኙት ውስጥ ደግሞ በባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የኾኑት አስማረ ሀይሌ ይገኙበታል። የሕዳሴ ግድቡ ብዙዎችን ከጨለማ ወደ ብርሃን የሚያሸጋገር መኾኑን በመረዳት ለአስራ አራት ዓመታት ድጋፍ አድርገዋል። ግድቡ እስኪጠናቀቅም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። በቀጣይ በሀገሪቱ በሚገነቡ የልማት ሥራዎች ላይ በንቃት እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።
ወይዘሮ ደብሬ አያሌው ግድቡ ከጀመረ ጀምሮ ድጋፍ እያደረጉ መኾኑን ገልጸዋል። የግድቡ ግንባታ በርካታ እናቶችን ከጭስ የሚያላቅቅ በመኾኑ ግንባታው እስከሚጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። የአሁኑ ትውልድ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት በሀገሩ ጉዳይ በጋራ እንዲቆም መክረዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የአማራ ክልል ማስተባባሪያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓባይነህ ጌጡ እንዳሉት በ2017 ዓ.ም ከማኅበረሰቡ ለመሰብሰብ ከታቀደው 100 ሚሊዮን ብር እስከ አሁን 90 ሚሊዮን ብር ማሰባሰብ ተችሏል።
ባለፉት አስራ አራት ዓመታት ደግሞ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ በክልሉ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ድርጅቶች እና ልዩ ልዩ የገቢ ማስገኛ መንገዶች ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ተሰብስቧል ብለዋል። ግድቡ በደለል እንዳይሞ ደግሞ የክልሉ ሕዝብ በአፈር እና ጥበቃ ሥራ 38 ቢሊዮን ብር የሚገመት የጉልበት አስተዋጽኦ ማበርከቱን ነው የገልጹት።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኀላፊ ፍቅርተ ታምር እንዳሉት ባለፉት አስራ አራት ዓመታት ኢትዮጵያውያን 23 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ለግድቡ አበርክተዋል ። ከዚህ ውስጥ ደግሞ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮኑ የአማራ ክልል ድርሻ መኾኑን ገልጸዋል። መላው ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ እውን መኾን ያደረጉት ተሳትፎ ግዙፍ የልማት ሥራዎችን በራስ አቅም መሥራት እንደሚቻል ለዓለም ማሳየት መቻሉንም ገልጸዋል።
ከገንዘብ፣ ከጉልበት እና ከዕውቀት ድጋፍ ባለፈ ለግድቡ ዲፕሎማት ኾኖ መሥራት በመቻሉ የአሸናፊነት መንፈስን መላበስ ተችሏል ብለዋል። በቀጣይም በጣና ላይ የተጋረጠውን እምቦጭ በመረባረብ ማስወገድ ከዚህ ትውልድ ይጠበቃል ብለዋል። ግድቡን ከደለል በመጠበቅ ዘላቂነቱን ለማረጋገጥም የተፋሰስ ልማት ሥራ ላይ ማተኮር እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!