
ወልድያ፡ ሰኔ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት 4ኛ ዙር 12ኛ ዓመት 38ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል። የምክር ቤት አባላት በከተማ እና መሠረተ ልማት አገልግሎት የሚነሱ ዘርፈ ብዙ የሕዝብ ጥያቄዎች የመልካም አሥተዳደር ችግር ኾነው ቀጥለዋል ብለዋል።
በመንግሥት አቅም ሊፈቱ የሚችሉትን በመፍታት የኑሮ ውድነት መንስኤዎችን፣ ሕገወጥ የነዳጅ ግብይት እና የመሬት ወረራን ለመከላከል መሪው እና ባለሙያው በቁርጠኝነት ሊሠራ እንደሚገባ አመላክተዋል። የአካባቢውን ሰላም ለማጽናት ከሕዝቡ ጋር የተጀመረው የቅንጅት ሥራ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት።
ለከተማዋ ዕድገት እና አሁን የተገኘውን ሰላም ለማጽናት የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል። የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ዓለማየሁ ነጋ የከተማውን ልማት በማፋጠን የኮሪደር ልማት፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ፧ የድልድይ ሥራዎች፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የሌማት ትሩፋቶች፣ ትምህርት ቤቶች ዙሪያ የአጥር ግንባታ እና በሌሎችም ዘርፎች አበረታች ጅምር ሥራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ከሕዝቡ ፍላጎት አኳያ በርካታ ሥራ ይጠበቃል ነው ያሉት።
ሕገወጥ ግንባታን፣ የመሬት ዘረፋን ማስቀረት እንደሚገባ እና አቅምን አሟጦ ገቢ መሠብሠብ ላይ መሠራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል። የወልዲያ ከተማ አሥተዳር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች እንዲጠናቀቁ የምክር ቤት አባላት ድጋፋቸውን ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
በተለይም በመንገድ እና በኮሪደር ልማት ሥራ ወሰን ማስከበር ላይ የኅብረተሰቡ ትብብር እንዲጠናከር አሳስበዋል። ሕገ ወጥነትን ለመከላከል በየደረጃው ያለ መሪ የድርሻቸውን እንዳልተወጣም ጠቅሰዋል።
ቦታ አጥረው እና ሕንጻ ጀምረው ለዓመታት የቆሙ ባለሀብቶች በአጭር ጊዜ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማበረታታት እንደሚገባም ነው የተናገሩት። በእያንዳንዱ የሕዝብ የልማት ሥራ ላይ የሚመለከታቸው መሪዎች እና ባለሙያዎች ሥራቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት። ምክር ቤቱ የታሪፍ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ እና ልዩ ልዩ ሹመቶችን በማጽደቅ ውሎው ተጠናቅቋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን