
ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የአሻጋሪ እድገት እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ ዙሪያ ሲሰጥ የነበረው የመሪዎች ሥልጠና ተጠናቅቋል። በሥልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አሻጋሪ ዕድገቱ እና የዘላቂ ልማት ዕቅድ ሥልጠናው አንድነትን እና የባለቤትነት ስሜትን የፈጠረ መኾኑን ተናግረዋል። የባለቤትነት ስሜት መያዝ ዕቅዱን ለመተግበር መንገድ መኾኑንም ገልጸዋል።
ሥልጠናው ለስትራቴጂክ ዕቅድ እና ለተቋማዊ ዕቅድ ግብዓት የተወሰደበት መኾኑንም ተናግረዋል። ውጤታማ ለመኾን ቆራጥ አመራር ይጠይቃል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የችግሩ ሥፋት በመደበኛ የአመራር ሂደት አይፈታም፣ ቆራጥ የአመራር ስልትን መጠቀም ይገባል ነው ያሉት። በሀገር ላይ ተሻጋሪ ለውጥ ያመጡ መሪዎች ጨከን ያለ እና ቆራጥ የአመራር ሂደትን ተጠቅመዋል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ እኛም ከችግር ለመውጣት ቆራጥ አመራር ያስፈልገናል ብለዋል።
የቁጭት ዕቅድ ያስፈለገንም መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ስላስፈለገን ነው ብለዋል። ብዙ ጊዜ በውስጥ ችግራችን ላይ ትኩረት እናድርግ ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ከደረሰው ችግር ትምህርት በመውሰድ ችግሮችን መቅረፍ ይገባል ነው ያሉት። ችግሮችን ውጫዊ በማድረግ ብቻ የሚፈታ ችግር እንደሌለም አንስተዋል።
ለዘመናት እየተንከባለሉ የመጡ ችግሮችን መረዳት እና መፍትሔ ማበጀት እንደሚገባም አመላክተዋል። የሕዝብ ዋነኛ ችግር የኾነውን ድህነትን ማቅለል እንደሚገባም ገልጸዋል። ድህነት ላይ የጸና አቋም በመያዝ ለመፍትሔው መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት። ጠንካራ ምጣኔ ሃብት እና ጠንካራ ተቋማትን መገንባት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
ከችግሩ በዘላቂነት ለመውጣት እና ጸጋን ተጠቅሞ ማኅበረሰብን ለማበልጸግ ዕቅዱ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ዕቅዱ ከሀገራዊ ዕቅዱ ጋር የተስማማ መኾኑንም ተናግረዋል። ሰላም እና ፍትሕን ከዕድገት ጋር ማያያዝ እንደሚገባም አመላክተዋል። ፕሮጀክት ላይ መሠረት ያደረገ የችግር አፈታት ሥራ መሥራት እንደሚገባም አንስተዋል። ዕቅዱን ስኬታማ ለማድረግ እንችላለን የሚለውን ወኔ መላበስ አለብን ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ያለንን ብዙ ሃብት ተጠቅመን ማሳካት እንችላለን ነው ያሉት። መጨነቅ ያለብን ሕዝባችንን እንዴት አድርገን መጥቅም አለብን? የሚለው ላይ ነው ብለዋል።
ሕዝብን የምንጠቅመው እሴት በሚጨምር አስተዋጽኦ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ብዙ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፣ ነገር ግን “ለሕዝባችን ፍላጎት ራሳችንን ማስገዛት አለብን” ነው ያሉት። ለተቋም ፍላጎት ራስን ማስገዛት እንደሚገባም ተናግረዋል።
“የብዙዎች ችግር መፍትሔ ያለው ከጉያችን ውስጥ ነው፣ ሌላ ቦታ አንፈልግ” ነው ያሉት። በችግር ውስጥ በመጽናት በታሪክ ውስጥ የሚታወስ ሥራ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። በታሪክ ትልቅ ስም ያላቸው መሪዎች ስማቸው የገነነው በችግር ውስጥ በመጽናታቸው እንደኾነም አንስተዋል።
አንድ በመኾን ለጋራ ግብ መሥራት ይገባል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ታላላቅ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል። ሁሉም መሪዎች ስትራቴጂክ እና ኦፕሬሽናል ዕቅድ ማቀድ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። የ90 ቀናት ዕቅድ እንዲያቅዱም አስገንዝበዋል። የለውጥ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል።
ዘጋቢ ፦ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን