
ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከአዘርባጃን ሪፐብሊክ የፐብሊክ ሰርቪስ እና ማኅበራዊ ፈጠራ ተቋም ሊቀ መንበር ኦልቪ ሜዲዬቭ ጋር ተወያይተዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ ከአዘርባጃን ሪፐብሊክ የፐብሊክ ሰርቪስ እና ማኅበራዊ ፈጠራ ተቋም ሊቀ መንበር ሚስተር ኦልቪ ሜዲዬቭ እና በኢትዮጵያ የአዘርባጃን አምባሳደር ሩስላን ናሲቦቭ ጋር ኢትዮጵያ እና አዘርባጃን በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውን ገልጸዋል።
ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎቹ በቅርቡ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት የኾነውን ሞሰብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን መጎብኘታቸውንም አንስተዋል። ኢትዮጵያ ይህን አገልግሎት በማስጀመር የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎትን ለማዘመን እና ለማቀላጠፍ እያከናወነች ያለችው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን ነግረውኛል ነው ያሉት።
በተጨማሪም ሊቀ መንበሩ ከሁለት አመት በፊት ኢትዮጵያን ሲጎበኙ ያዩት የአዲስ አበባ ከተማ ገፅታ በእጅጉ የተለወጠ መሆኑ እንዳስገረማቸው ተናግረዋል ብለዋል። በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በመገኘትም የኢትዮጵያን ታሪካዊ እሴቶች የሚያሳየውን ሙዚየም ጎብኝተዋል። በዚህ ስፍራ የተመለከቷቸው ነገሮችም ዕጅግ አስደናቂ መሆናቸውን ገልፀውልኛል ብለዋል በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን