
ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ድጋፍ አሠባሣቢ እና አሥተባባሪ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የምሥጋና እና ዕውቅና መርሐ ግብር አካሂዷል። በመርሐ ግብሩ የተገኙት የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) እንዳሉት ዓባይ ለአማራ ሕዝብ ወንዝ ብቻ ሳይኾን ሃይማኖቱ፣ የሥነ ቃሉ መነሻ እና የጀግንነቱ መገለጫ ነው።
ይህ የሕዝቡ ሁለንተናዊ የኾነ ሃብት አሁን ላይ በኢትዮጵያውያን ሁለንተናዊ ተሳትፎ “ግንድ ይዞ ይዞራል” ከሚል እንጉርጉሮ ወጥቶ ኢኮኖሚ የሚያመነጭ፣ ብርሃን የሚያበራ ሃብት ኾኗል ብለዋል። ዓባይ በራስ አቅም ከመገንባት ባለፈ የኢትዮጵያን ፖለቲካ አቅም ያሳየ፣ የሀገሪቱን ዲፕሎማሲ ደግሞ ወደ ቀይ ባሕር ያሸጋገረ፣ በፍትሐዊነት የመጠቀም መብትንም ለዓለም ያሳየ መኾኑን ገልጸዋል። ይህ በፍትሐዊነት የመጠቀም መርህ ባሕል ኾኖ ሊቀጥል ይገባልም ብለዋል።
ከገንዘብ እና ከጉልበት አበርክቶ ባለፈ የተፈጥሮ ሚዛን እንዳይዛባ ማኅበረሰቡ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ደኖችን በመትከል ግድቡን ከደለል የመጠበቅ ታሪካዊ ኀላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል። የተያዘውን ልማት አጠናክሮ ለመቀጠል ማኅበረሰቡ የውስጥ ሰላሙን በማስጠበቅ አንድነቱን ማጠናከር እንደሚገባውም አስገንዝበዋል። የተፈጠሩ ችግሮችንም በውይይት የመፍታት ባሕልን ማዳበር ይገባል ብለዋል።
በጫካ የሚገኙ ወገኖች የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ እና በክልላቸው ብሎም በሀገራቸው ልማት እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል። የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) የሕዳሴው ግድብ ግንባታ የአማራ ክልል ሕዝብ አንድነትን ያሳየበት መኾኑን ገልጸዋል።
የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን ችግር ለመፍታት መንገድ የጠረገ መኾኑንም አስገንዝበዋል። ማኅበረሰቡ በታላቁ ግድብ ያሳየውን አንድነት በሌሎች የልማት ሥራዎች አጠናክሮ ሊቀጥልም ይገባል ብለዋል። አሁን ላይ ሀገሪቱ ከገጠማት ችግር ለመውጣት በአንድነት መቆም ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን