
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 21/2012 ዓ.ም (አብመድ) በገጠር መሬት ኢንቨስትመንት የሚሰማሩ 75 አዳዲስ አልሚዎችን መለየቱን የአማራ ክልል ገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ አስታወቀ፡፡ መመዘኛውን ያለፉ ባለሀብቶች በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲሰማሩም አሳሰቧል፡፡
በ2012/13 የመኸር ወቅት በኮሮና ወረርሽኝ፣ በበርሃ አንበጣ መንጋ እና በሌሎች ችግሮች ሊፈጠር የሚችለውን የምርት ቅናሽ ለማካካስ የአማራ ክልል መንግሥት 60 ሺህ ሄክታር መሬት ለአዲስ አልሚዎች ለማስተላለፍ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ በዘርፉ ለመሰማራት ከቀረቡት አልሚዎች መካከልም የተሻለ የግብርና ቴክኖሎጂና የፋይናንስ አቅም ያላቸውን 75 አልሚዎች መለየቱንም ቢሮው አስታውቋል፡፡
ከቢሮው የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው አልሚዎቹ እስከ ግንቦት 30/2012 ዓ.ም ውል ገብተው በቀጥታ ወደ ሥራ እንዲገቡ እየተሠራ ነው፡፡
ተጨማሪ ምርት ለማግኘት ለአልሚዎች የሚተላለፉት መሬቶች በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ፣ ቋራ እና ምዕራብ አርማጭሆ፣ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጠገዴ ወረዳ፣ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዚገምና ጃዊ፣ በምሥራቅ ጎጃም፣ በምዕራብ ጎጃም እና በሰሜን ሸዋ ዞኖች ነው የሚገኙት፡፡ ከተመረጡት ቦታዎች መካከል ተወዳዳሪ ያልቀረበላቸው ቦታዎች መኖራቸውን የቢሮው የገጠር መሬት ኢንቨስትመንት ዳይሬክተር ጥጋቡ በላይ አስታውቀዋል፡፡ ለመኸሩ የግብርና ሥራ ለማዋል ካልተመለመሉት ተወዳዳሪዎቸ መካከል የተሻለ አንጻራዊ አቅም ያላቸው አልሚዎች እንዲሰማሩ እየተሠራ እንደሆነም ታውቋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ቢሮው ጊዜያዊ መመሪያ በማዘጋጀት የአፈጻጸም ችግር የነበረባቸውን ኢንቨስተሮች መሬት በመቀማት፣ በአበዳሪ ተቋማት የተያዙ፣ በፍርድ ቤት የታገዱ እና ሳይለሙ የተቀመጡ መሬቶችን ጨምሮ 60 ሺህ ሄክታር መሬት ነው ለአልሚዎች የሚያስተላልፈው፡፡
ጊዜያዊ መመሪያው የተዘጋጀው የመኸር ወቅት ሳያልፍ አልሚዎችን ወደ ሥራ ለማሰማራት ነው፡፡ መመሪያው የአገልግሎት ክፍያን የሚያስቀር በመሆኑ ግን ክልሉ 12 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ደርሶበታል፡፡ ምንም እንኳን የምርት እጥረቱን በምን ያህል እንደሚያካክሰው መግለጽ ባይችሉም የግብርና ቴክኖሎጂን እና ዘመናዊ የግብርና አሠራርን በመጠቀም የተሻለ ምርት እንደሚያስገኝ ግን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡ አልሚዎች በመኸሩ እንዲዘሩም ቢሮው ከግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር እስከ ወረዳ ባለው መዋቅሩ ድጋፍ እና ክትትል ያደርጋል፡፡ አልሚዎች ጥሩ የሚሠሩ ከሆነ ወደ መደበኛ ውል እንዲገቡ እንደሚደረግና ውጤታማ ካልሆኑ ደግሞ ውላቸው እንደሚቋረጥም ተገልጿል፡፡
በቀጣዩ መኸር በአማራ ክልል 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሰብል እንደሚሸፈን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገልጿል፡፡ 127 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱንም በቢሮው የሰብል ልማት ዳይሬክተር አለባቸው አሊጋዝ አስታውቀዋል፡፡ ይህንን ለማገኘት የሚያስችሉ የግብርና ማዕቀፍ (ፓኬጂ) ሥራዎች ቀደም ብለው መሠራታቸውንና ለባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱንም ተናግረዋል፡፡
በወቅቱ ለማስገባተ ከታቀደው የአፈር ማዳበሪያ 65 በመቶ የሚሆነው ወደ ክልሉ ገብቶ ለአርሶ አደሮች እየተሠራጨ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ስልጠናውን ለቀበሌ ባለሙያዎችና ለአርሶ አደሮች ማድረስ አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡ በቀሪ ጊዜያት ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተጋላጭ በማያደርግ መልኩ ስልጠና ለመስጠት እንደሚሠራም አቶ አለባቸው ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ፎቶ፡- ከፋይል
