ጤና ቢሮ የሕጻናት ክትባትን የሚያደርሱ እና የሚያስተባብሩ ወጣቶችን አሠልጥኖ ሊያሰማራ ነው።

8

ደሴ: ሰኔ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ከአጋሮች ድርጅቶች ጋር በመተባበር የክትባት ተደራሽነትን ለማስፋፋት የሕጻናት ክትባትን የሚያደርሱ እና የሚያስተባብሩ ወጣቶችን ለ45 ቀናት በክትባት እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አሠልጥኖ በማስመረቅ የሞተር ርክክብ አካሂዷል።

ሠልጥነው የሞተር ብስክሌት ከተረከቡ ወጣቶች መካከል ከምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ የመጣው ወጣት ይልቃል አዳነ በወሰደው ሥልጠና መሠረት ለማኅበረሰቡ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት እንደተዘጋጀ ለአሚኮ ተናግሯል።ሌላኛው አስተያየት ሰጭ ከሰሜን ሽዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ የመጣው ወጣት የኢየሱስወርቅ ይግለጡ በወረዳው መኪና የማይገባበት በጣም አስቸጋሪ መልክዓ ምድር መኖሩን አስታውሶ የክትባት ዕድል ላላገኙ ሕጻናት መድረስ በመቻሉ ደስተኛ መኾኑን ገልጿል።

ከተሰጠው ኀላፊነት በተጓዳኝም የሞተር ብስክሌቱን በመጠቀም ሌሎች ራሱን ለመለወጥ የሚያስችሉ ሥራዎችን እንዲሠራ ዕድል መሰጠቱ ነው የተናገረው። በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የእናቶች፣ ሕጻናት አና የአፍላ ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መልሰው ጫንያለው በክልሉ ከ800 ሺህ በላይ ሕጻናት ክትባት አለማግኘታቸውን ገልጸው በዚህ ወቅት 200ሺህ ያህሉን መከተብ መቻሉን አስረድተዋል።

እነዚህ ወጣቶች ወደ ሥራ ሲገቡ የክትባት ተደራሽነት ችግሩን እንደሚቀርፉም ነው ያብራሩት። የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ገስጥ ጥላሁን የክልሉ የአምስት ዓመት የጤና ስትራቴጅክ ዕቅድ ዋና ዓላማ ፍትሐዊ እና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ማዳረስ በመኾኑ ይህ ፕሮግራም ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው አስገንዝበዋል።

በክልሉ ባሉ 10 ወረዳዎች 40 ወጣቶችን በመመልመል 40 የሞተር ብስክሌቶች ተሰጥቷቸው ከጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ጋር አብረው እንዲሠሩ ለማድረግ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል። ወረዳዎች የተመረጡበትን መሥፈርት ሲያስረዱ የትራንስፖርት ተደራሽነታቸው ዝቅተኛ መኾኑ እና የወረዳዎች መልክዓምድራዊ አቀማመጥ ለተሽከርካሪዎች እጅግ አስቸጋሪ በመኾኑ ነው ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የክትባት ተደራሽነታቸው ዝቅተኛ ነው። ስለኾነም ሕጻናትን የሚያጠቃ ተደጋጋሚ ወረርሽኝ እንደሚስተዋልባቸውም ገልጸዋል። ለሥራው የተመለመሉ ወጣቶችም በየወረዳዎቹ በሥነ ምግባራቸው አርዓያ የኾኑ፣ ኅብረተሰቡን ለማገልገል ቁርጠኛ የኾኑ እና በማኅበረሰቡ ዘንድ ምስክርነት የተሰጣቸው ናቸው ብለዋል።

ኀላፊው ወጣቶቹ በወር ውስጥ 10 ቀናት ክትባት የማድረስ ሥራ ከሠሩ በኋላ ቀሪውን የሞተር ብስክሌቱን በመጠቀም የግል ሥራቸውን እንዲሠሩ ይደረጋል፤ ይኸውም ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል።
ከአምስት ዓመት በኋላ ደግም አፈፃፀማቸው እየታየም ሞተሩን ለግላቸው እንዲወስዱት ይደረጋል ብለዋል።

ተግባሩን ዘላቂ ለማድረግ እና ወደሌሎች አካባቢዎችም ለማስፋት በቁርጠኝነት ሊሠራ ይገባል ሲሉ አቶ ገስጥ አሳስበዋል። መርሐ ግብሩ በሌሎች ክልሎች ሲተገበር የቆዬ ሲኾን በአማራ ክልል ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የተደረገ መኾኑ ተመላክቷል።

ዘጋቢ፦ አንተነህ ፀጋዬ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleዝናብ አጠር በኾኑ አካባቢዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች የዝናብ ውኃ ማጠራቀሚያ ቴክኖሎጅዎችን በማስተዋወቅ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ ነው።
Next articleየታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በራስ አቅም ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መገንባት እንደሚቻል የታየበት ነው።