
አዲስ አበባ: ሰኔ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 6ኛው የአፍሪካ የውኃ ማቆር ፕሮጀክት በሰሜን ሽዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አረርቲ ከተማ ተጀምሯል። “የኢትዮጵያ የዝናብ ውኃ አጠቃቀም ማኅበር” በኢትዮጵያ ሕጋዊ ሰውነት ያገኘ መንግሥታዊ ያልኾነ ተቋም ነው።
ማኅበሩ ዝናብ አጠር አካባቢዎች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ፕሮጀክት መኾኑን የማኅበሩ ሥራ አሥኪያጅ ምንያህል ፍቃዱ አንስተዋል። ማኅበሩ በተለይም ዝናብ አጠር በኾኑ የአማራ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልል አካባቢዎች ለሚገኙ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አርሶ አደሮች የዝናብ ውኃ ማጠራቀሚያ ቴክኖሎጅዎችን የማስተዋወቅ እና የውኃ መሠባሠቢያ ገንዳዎችን የመገንባት ሥራ እያከናወነ ነው ብለዋል።
ማኅበሩ ከቻይናው ፋውንዴሽን ፎር ሩራል ዴቬሎፕመንት እና ኤክስ ኤም ጂ ካንፓኒ ባገኘው የገንዘብ ደጋፍ አርሶ አደሮች የዝናብ ውኃን በማቆር ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚ እንዲኾኑ እየተሠራ እንደኾነም አስረድተዋል። ከአሁን በፊት በውኃ እጥረት ለበርካት ችግር የሚጋለጡ አርሶ አደሮች የዝናብ ውኃን በጓሯቸው ሠብሥበው የተለያዩ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን በማልማት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።
እሰካሁን ከ240 በላይ የውኃ ማጠራቀሚያ ታንከሮችን ተደራሽ በማድረግ ከ2 ሺህ በላይ አርሶአደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። የዝናብ ውኃን በማቆር የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት እና ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መኾኑን የኤክስ ኤም ጂ ካንፓኒ አስተባባሪ ሚስተር ሞንግ ሻንጋ ገልጸዋል።
በቀጣይም ካንፓኒው የተለመደ ድጋፉን አጠናክሮ ለመቀጠል ቁርጠኛ መኾኑን አረጋግጠዋል።አርሶ አደር ተስፋዬ ንጉሴ በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የሳማ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ባለፈው ዓመት በፕሮጀክቱ ታቅፈው ተጠቃሚ ከኾኑ የአካባቢው አርሶ አደሮች አንዱ ናቸው።
ከአሁን በፊት የዝናብ ውኃ በተገነባላቸው ታንከር በመሠብሠብ የተለያዩ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን ማልማታቸውን አንስተዋል። በዚህም ከራሳቸው የምግብ ፍጆታ ባለፈ ምርቱን ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መኾናቸውን ነው የገለጹት።
የታቆረው ውኃ በንጽህና እና በአግባቡ በመጠቀም ለእንስሳት መጠጥ እና ለተለያዩ አገልግሎቶች እየተጠቀሙ ነው። በዚህው ቀበሌ ነዋሪ የኾኑት አርሶ አደር ፈጠነ ታምራት እና በላይ ወዳጁ በዚህ ዓመት በፕሮጀክቱ መታቀፋቸውን አንስተዋል። በተገነባላቸው ታንከር የዝናብ ውኃን በማቆር ማንጎ፣ አቦካዶ፣ ፓፓያ፣ ቡና፣ ሌሎች አትክልት እና ፍራፍሬዎችን ለማልማት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የዝናብ ውኃ አጠቃቀም ማኅበር፣ የቻይናው ፋውንዴሽን ፎር ሩራል ዴቬሎፕመንት እና ኤክስ ኤም ጂ ካንፓኒ የአካባቢውን ማኅበረሰብ በግብርናው ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ እያበረከቱት ስላለው አስተዋጽኦ አመሥግነዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን