
ባሕር ዳር: ሰኔ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ሴት የሰላም አምባሳደሮችን ማደራጀት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ” በሚል መሪ መልዕክት ለሴት አምባሳደሮች ለሁለት ቀናት ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ተጠናቅቋል። በአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሴቶች ክንፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኢለኒ ዓባይ ሰላም እንዲመጣ ሁሉም ስለ ሰላም መመካከር ከቤቱ ሊጀምር ይገባል ብለዋል።
ሁሉም ሴቶች ስለነገው አስባችሁ ለሰላም ግንዛቤ መፍጠር፣ አደረጃጀቶችን ማጠናከር እና ግንዛቤ መፍጠር ይኖርባችኋል ነው ያሉት። ከሥልጠናው የወሰዳችሁትን አቅም በመጠቀም ወደ ተግባር መግባት፣ ተሞክሮ መቀመር እና ማስፋት እንዲሁም ለሌሎች አደረጃጀቶች ጠንካራ ድጋፍ እና ክትትል ማድረግ ይጠበቅባችኋል ብለዋል።
በሰላም ሚኒስቴር የሥርዓተ ጾታ መሪ ሥራ አሥፈፃሚ ወጋየሁ ቢያድግልኝ የተሰጠውን ሥልጠና በመጠቀም የሰላም አምባሳደሮችን በየደረጃው በማቋቋም መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል። ሴቶች ዕድል እንጂ አቅም እንዳላጡ የተናገሩት ሥራ አሥፈፃሚዋ ሰላምን ለማምጣት አሁን ላይ ሴቶች ከፍተኛ ዕድልም አቅምም አላቸው ብለዋል።
ከባሕር ዳር የመጡት የሥልጠናው ተሳታፊ ዘውዳለም ወረታው ሰላም ባለመኖሩ ሴቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ እንደኾነ ተናግረዋል። ግጭት እና አለመግባባት ለማንም አይጠቅምም፤ በዚህም ምክንያት ሠርቶ ለማደር አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው እና በየትኛውም አጋጣሚ ስለሰላም መምከር አለብን ብለዋል።
ይህንን ሥልጠና ወስደው በቀጣይም ስለሰላም መነጋገር፣ በየቤቱ ወስዶ ለሌሎችም ማካፈል እና ማሠልጠን ይገባል ነው ያሉት። ከደብረ ታቦር ከተማ የመጡት ሌላዋ የሥልጠና ተሳታፊ ቤተልሄም ክበቤ ሰላም ለሴቶች በተለይም ለሕጻናት ወሳኝ ነው፤ ሴቶች የሰላም አምባሳደሮች ናቸው ብለዋል።
ሰላሙ በደፈረሰ ጊዜ አሰቃቂ ነገሮችን ስለማየታቸው የተናገሩት ወይዘሮ ቤተልሔም ልጆች ያለአሳዳጊ፣ ወላጆች ያለጧሪ እንዲቀሩ ምክንያት እንደኾነም አስረድተዋል። ሁሉም ሰላም እንዲመጣ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ነው የተናገሩት። የተሰጠው ሥልጠና የእርስ በእርስ ትውውቅን እና ግንኙነትን ለማዳበር እና ልጆችን ለመምከር ዕድል ስለመፍጠሩ ነው ያብራሩት። በቀጣይ ሰላሙ የተረጋገጠ ክልል ለመፍጠር በቁርጠኝነት እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን