
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 21/2012 ዓ.ም (አብመድ) የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸውን እንዲበትኑ አስገድዷቸዋል፡፡
ተማሪዎቹን ከትምህርት ገበታቸው ማስተጓጎሉ አሉታዊ ተፅዕኖው የከፋ ቢሆንም ስለወረርሽኑ ግንዘቤ በመፍጠር ረገድ ወደ መልካም ዕድል እየቀየሩት ያሉ አሉ፡፡
ወደ ሰሜን ሸዋ ዞን በረኸት ወረዳ ባቀናንበት ወቅት ያገኘናቸው ከተለያዩ የሀገሪቱ አቅጣጫዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው የተመለሱ ተማሪዎች እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም፡፡ ተማሪዎቹ ለኅብረተሰቡ ስለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሚያወቁትን እያሳወቁ ነው፡፡
ተማሪ ሄኖክ ወርቁ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዓመት የጋዜጠኝነት እና ሥነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል ተማሪ ነው፡፡ ሄኖክ ወደ ትውልድ ቀዬው ከተመለሰ ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ስለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ቅድመ መከላከል ከመንግሥት እና ከጤና ባለሙያዎች የሚወጡ መልእክቶችን ለኅብረተሰቡ እያስገነዘበ ነው፡፡ የግንዛቤ ፈጠራውን በ‘ሚኒ ሚዲያ’፣ በገበያ እና ሰዎች በሚሰባሰቡባቸው ቦታዎች በመገኘት ከጓደኞቹ ጋር እንደሚሠሩም ተናግሯል፡፡ ከግንዛቤ ፈጠራ ጎን ለጎን ደግሞ የዚህ ዓመት ተመራቂ ተማሪ እንደመሆኑ መጠን ጥናታዊ ጽሑፉን እየሠራ ጊዜውን በአግባባቡ እየተጠቀመ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
ሌላኛው ያነጋገርነው ተማሪ አብርሃም ገብረኪዳን በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሦስተኛ ዓመት የሕግ ተማሪ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዳይጋለጥ ሰፈር ለሰፈር፣ በገበያ ቀን ከወረዳው መዲና መተህብላ ከተማ መግቢያና መውጫ አካባቢዎች እጅ እንዲታጠቡ ከማድረግ ጀምሮ የወረርሽኙን ቅድመ መከላከል መልእክቶች በድምጽ ማጉያ (ሞንታርቦ) ተጠቅመው እያስተላለፉ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ተማሪዎቹ በሚያደርጉት የቅስቀሳ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ወረዳ አስተዳደሩ፣ አማተር የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እና በጎ አድራጎት ማኅበራት እገዛ እንደሚያደርጉላቸውም ገልጿል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ሌሎች ተማሪዎችም ቅድሚያ ራሳቸውን መጠበቅ ኅብረተሰቡ ራሱን እንዲጠብቅ አርአያ በመሆን የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ መሥራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ በተለይም ለሕዝብ ደኅንነት ሲባል የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልእክቶች እንዲተገበሩ የዩነቨርሲቲ ተማሪዎች ያላቸው ሚና የጎላ በመሆኑ ይህንን ሚናቸውን እንዲጫወቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የበረኸት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ይደሰቱ ክፈተው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ስለወረርሽኙ የሚሰጠው ግንዛቤ የተሻለ እንዲሆን እያገዘ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ወረዳ አስተዳደሩም ለተማሪዎች ልፋት መሳካት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ እንደ ዋና አስተዳዳሪው ከበጎ ፈቃደኞቹ ተግባር ባሻገር ወረርሽኙን ለመከላከል በአፋር እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚገቡ ሰዎችን የሰውነት ሙቀት ልኬታ ምርመራ ይደረጋል፡፡ በተለይም በወረዳው የልማት ፕሮጀክቶች እየተሠሩ በመሆናቸው እና አካባቢው ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተጋላጭ በመሆኑ ቅድመ መከላከሉ ሥራ ላይ እንደሚረባረቡ ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡
