የአዕምሮ እድገት መዛባት (ኦቲዝ) መንስኤው ምንድን ነው?

28

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዕምሮ ዕድገት መዛባት (ኦቲዝም) የነርቭ እና የአንጎል ሥርዓት ዕድገት ችግር ነው፡፡ ችግሩ ከጨቅላነት ጀምሮ በማደግ ምንነቱ ሳይታወቅ ረጅም ጊዜ ሊያስቆጥር እንደሚችል ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የአዕምሮ ዕድገት መዛባት(ኦቲዝም) በተለያዩ ምክንያቶች ሊመጣ እንደሚችል ይነገራል። በዘር ተወራራሽነት ወይም በውል ላልተለየ ውጫዊ ተጽዕኖዎች ተጋላጭ መኾን የኦቲዝም የአዕምሮ ዕድገት መዛባትን ሊያመጡ ይችላሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ተላላፊ ያልኾኑ በሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠረ ባለሙያ፣ የክልሉ የአዕምሮ እና የዐይን ጤና ዋና ተጠሪ ፈቃዱ አድማስ (ዶ.ር) ኦቲዝም ከነርብ እና አንጎል አሠራር ሂደት ጋር ግንኙነት ያላው የዕድገት ችግር እንደኾነ ገልጸዋል። ሕመሙ ከሰዎች ጋር በሚደረግ ግንኙነት እና መስተጋብር የሚታወቅ ነው። ኦቲዝም ያለባቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ የተገደቡ እና ተደጋጋሚ ፍላጎቶችን ወይም ባህሪዎችን እንደሚያሳዩ ነው የገለጹት።

ለኦቲዝም አጋላጭ ነገሮች ምንድን ናቸው?

በቤተሰብ ወይም የቅርብ ዘመድ የኦቲዝም ተጠቂ ካለ፣ ዕድሜ ከገፋ በኋላ የሚወለድ ልጅ ለኦቲዝም እንደ አጋላጭ ተደርጎ ይወሰዳል። ልጆችን በጣም አቀራርቦ መውለድ፤ ያ ማለት ከሁለት ዓመት በታች በኾነ ልዩነት የተወለዱ ሕጻናት ይበልጥ ተጋላጭ ይኾናሉ።

እናት በእርግዝና ወቅት የተለያዩ መድኃኒቶችን የምትወስድ ከኾነ፣ ለኬሚካሎች ተጋላጭ ከኾነች፣ የአልኮል መጠጦችን በተደጋጋሚ የምትወስድ ከኾነችም ለችግሩ ተጋላጭ እንደኾነች ተደርጎ ይወሰዳል። ጊዜው ሳይደርስ መወለድ፣ በወሊድ ጊዜ ወይም ከተወለዱ በኋላ ለተለያዩ አደጋዎች መጋለጥ ማለትም ደም መፍሰስ፣ የተራዘመ ምጥ፣ የማጅራት ገትር በሽታ፣ የሚጥል ሕመም፣ የምግብ እጥረት ወዘተ ለኦቲዝም አጋላጭ ኹኔታዎች ተደርገው ይወሰዳሉ ።

ባለሙያው የኦቲዝም ምልክቶች አነስተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ተብለው እንደሚመደቡም አንስተዋል። በኦቲዝም የተጠቁ ሰዎች በቋንቋ ወይም በማኅበራዊ ግንኙነት ዕድገት ላይ ጉልህ የኾኑ መዘግየቶችን ያሳያሉ።

አንዳንድ ኦቲዝም ያለባቸው ሕፃናት የእንቅስቃሴ መዘግየት፣ የሚጥል በሽታ፣ የሆድ ድርቀት ወይም ተቅማጥ ምልክቶችን ያሳያሉ። የኦቲዝም ተጠቂዎች ከልክ ያለፈ ጭንቀት፣ ያልተለመደ ፍርሐት፣ ግትርነት፣ ትኩረት ማጣት ይገጥማቸዋል።

ያልተጠበቁ ስሜታዊ ምላሾች፣ ያልተለመዱ አመጋገቦች፣ ልማዶች እና ያልተለመደ እንቅልፍ እና ሌሎችም ምልክቶችን ሊያሳዩ ይችላሉ። ኦቲዝም ላለበት ሰው ከሚሰጠው ሕክምና መካከል የመድኃኒት፣ የሥነ ልቦና፣ የማኅበራዊ እና የባሕርይ ሕክምናዎች ተጠቃሾች ናቸው። የአዕምሮ ዕድገት መዛባትን በመንስኤነት የተጠቀሱትን ችግሮች በማስወገድ የተጋላጭነት ስጋቱን መቀነስ እንደሚቻልም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleበወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የትራፍሪክ እንቅስቃሴ ቁጥጥርን ለማዘመን እየተሠራ ነው።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከአሜሪካ ማሪን ኮርፕስ ጄኔራል እና አፍሪኮም አዛዥ ጄነራል ማይክል ላንግሌይ ተወያዩ።