
ሁመራ፡ ሰኔ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ባለሥልጣን ከ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ያደረገባቸውን ስድስት ሞተር ሳይክሎች ለወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ጽሕፈት ቤት ሰጥቷል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ለምለሙ ባየህ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ዞኑ ነጻነቱን ካገኘበት ጊዜ ጀምሮ የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን በባለሥልጣኑ በኩል በርካታ ድጋፎች ተደርገዋል ብለዋል።
ከባለሥልጣኑ የሚሰጡ ድጋፎቾን በትክክል ጥቅም ላይ በማዋል ጤናማ የትራፍሪክ እንቅስቃሴ ለመፍጠር እየሠራን ነው ያሉት ኀላፊው በዚህም በርካታ ለውጦች መታየታቸውን አስረድተዋል። ይሄንን ተግባር የበለጠ ለማሳግ ይረዳን ዘንድ ከ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ያደረገባቸውን ስድስት ሞተር ሳይክሎች የክልሉ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ባለስልጣን ድጋፍ አድርጎልናል ነው ያሉት።
እነዚህን ሞተር ሳይክሎች በዞኑ ከፍተኛ የትራፊክ እንቅስቃሴ ላለባቸው እና በሥራ አፈጻጸማቸው ለተሻሉት አካባቢዎች ማሥረከባቸውንም ገልጸዋል። የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የዞኑ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ጽሕፈት ቤት ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በቅንጅት በመሥራት ሕግ እንዲከበር እና ሰላም እና ጸጥታ እንዲሰፍን እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
ሞተሮቹን በድጋፍ የሰጠውን የክልሉ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ያመሰገኑት ኮሎኔል ደመቀ ዞኑ የተሰጡትን ሞተሮች በአግባቡ በመጠቀም የተሻለ የትራፊክ እንቅስቃሴ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባውም አስረድተዋል። የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው የክልሉ መንግሥት ባለፉት አምስት የነፃነት ዓመታት በሰው ኀይል፣ በገንዘብ እና በቁሳቁስ በቻለው መጠን ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
ዞኑን ለማደራጀት እና ለማጠናከር እየተደረገ ካለው ድጋፍ መካከል የሞተር ድጋፉ አንዱ መኾኑንም ጠቅሰዋል። በዞኑ እየተከናወኑ ያሉ የልማት እና ሌሎች ተግባራት ያለ ክልሉ ድጋፍ የሚቻሉ አልነበሩም ያሉት አቶ አሸተ የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን ክልሉ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል።
የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ጽሕፈት ቤቱ የሚደረጉለትን ክትትል እና ድጋፎች በመጠቀም ሲስተምን የማዘመን ሥራ እያከናወነ ነው ብለዋል። ሁሉም ተሽከርካሪዎች በሕጋዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ፣ በአሠራር እና በሕግ ሕዝብን እንዲያገለግሉ ጠንካራ አሠራር እየተዘረጋ መኾኑንም ገልጸዋል።
ሞተር ሳይክሎቹ በትራፊክ እንቅስቃሴ ምክንያት የሚያጋጥሙ አደጋዎችን እና ወንጀሎችን ለመቆጣጠር እንደሚያግዙ በርክክቡ ወቅት ያገኘናቸው የማይካድራ ከተማ ከንቲባ ሙሉጌታ መብራቱ ተናግረዋል። ከተማ አሥተዳደሩ በትኩረት ከሚሠራባቸው ዘርፎቾ መካከል ትራንስፖርት አንዱ መኾኑን አንስተዋል። ባለሙያዎቹ ሕግን ለማስከበር እና ጤናማ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር ለማድረግ ሞተሮቹ እንደሚያግዟቸው ነው የገለጹት።
የሁመራ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ እንኳየነህ ሙሉ በከተማዋ በርካታ የተሸክርካሪ ፍሰት መኖሩን ጠቅሰዋል። ይሄንን ፍሰት ለመከታተል እና ለመቆጣጠር የሞተር ሳይክል ድጋፍ መደረጉ ወሳኝ ነው ብለዋል። ከተማ አሥተዳደሩ የተሰጠው ሞተር ቀልጣፋ እና ውጤታማ ሥራ እንዲሠራ ያስችለዋል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን