
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 13/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዓመቱን ሙሉ አረንጓዴ ግቢ ያለው ዩኒቨርሲቲ ነው። በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የግቢውን አረንጓዴ መልክ አይተው “ዩኒቨርሲቲው ግቢውን ለመማር ማስተማር ምቹ ለማድረግ አስተማሪ እና አኩሪ ሥራ ሠርቷል” በማለት ውበቱን መስክረውለታል። ከውበት ባለፈ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ችግር እንዲፈታ እና በዓለም ደረጃ የሚወዳደሩ ልሂቃንን እንዲያፈራም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማትጊያ መልዕክት አድርሰውት ነበር። በውበቱ ብዙዎች የመሰከሩለት፣ ዕውቀት እና አገልግሎትን እንዲያስፋፋም አደራ የተጣለበት ይህ ዩኒቨርሲቲ ምን የተግባር ሥራዎችን እያከናወነ ይኾን?
በደጋዋ ምድር ላይ የተመሠረተው አረንጓዴው ግቢ በአራት ኮሌጆች እና በ22 የትምህርት ክፍሎች 1 ሺህ 500 መደበኛ ተማሪዎችን በመቀበል በ2010 ዓ.ም ነበር የመማር ማስተማር ሥራውን የጀመረው። ዩኒቨርሲቲው ገና ሲመሠረት ጀምሮ ከመማር ማስተማር እና ከግንባታ ጎን ለጎን የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን በትጋት ይሠራ ስለነበር የአሁኑን ማራኪ ገጽታውን ተጎናጽፏል። ይህ ግብሩም “አረንጓዴው ግቢ” የሚል ጥሩ ስም አስገኝቶለታል እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ።
የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጋርዳቸው ወርቁ (ዶ.ር) አረንጓዴው ግቢ በዚህ ወቅት 17 ሺህ ተማሪዎችን እና 3 ሺህ ሠራተኞችን በአጠቃላይ ከ20 ሺህ በላይ የዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰቦች በውስጡ አቅፎ ይዟል ብለዋል። እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ አሁን ላይ በአጠቃላይ በ109 ፕሮግራሞች ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ መኾኑንም ጠቁመዋል።
የዩኒቨርሲቲው ዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የኾኑ ልሂቃንን የማፍራት ጉዞ የተሳካ ይኾን ዘንድ መምህራን እና መላው የዩኒቨርሲቲው አሥተዳደር እየተጉ እንደሚገኙም ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲውን ለመማር ማስተማር ምቹ የማድረግ ሥራ ተቀዳሚ ተግባር መኾኑንም አንስተዋል።
ከትምህርት ሚኒስቴር የወረዱ የትምህርት ጥራት ማስጠበቂያ አሠራሮችን በመከተል ዩኒቨርሲቲው የማስተማር ሥነ ዘዴን በማሳደግ፣ የመምህራንን አቅም በማጎልበት፣ የግምገማ ሥርዓትን በማጠናከር እና የትምህርት ክፍሎችን በአግባቡ በመሸፈን ለጥራት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል።
በ2017 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያስመዘገቡት ውጤት ዩኒቨርሲቲው ለመማር ማስተማር ሥራ እና ለትምህርት ጥራት የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ መኾኑንም ጠቅሰዋል። በመደበኛ መርሐ ግብር በ48 ፕሮገራሞች የመውጫ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች ውስጥ 92 በመቶው ፈተናውን አልፈዋል። ከ48ቱ ፕሮግራሞች በ32 ፕሮግራሞች ሲማሩ ቆይተው የተፈተኑ ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ፈተናውን አልፈዋል።
ይህ ውጤት ሊመዘገብ የቻለው ተማሪዎች ለማወቅ እና ለዓላማቸው ብቻ መጣራቸው፣ መምህራን ሙሉ ጊዜ እና ዕውቀታቸውን ሳይሰስቱ ለተማሪዎች መስጠታቸው እና የዩኒቨርሲቲው መሪዎችም አሥፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በማድረጋቸው ነው ብለዋል።
እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በአረንጓዴ ተክሎች፣ በአፕል፣ በደጋ ቡና እና በተለያዩ አትክልቶች የታጀበ እና ለዕይታ ማራኪ ይኾን ዘንድ የዩኒቨርሲቲው ግብርና ኮሌጅ በትኩረት እየሠራ ነው፤ ውጤትም አስመዝግቧል ነው ያሉት። ከ10 ሚሊዮን በላይ የሚኾኑ የተለያዩ ችግኞችን ለአካባቢው ማኅበረሰብ በነጻ አከፋፍለናልም ብለዋል። ይህም በአካባቢው ያለውን የአረንጓዴ ልማት ሥራ የሚደግፍ ተግባር መኾኑን አብራርተዋል።
“ምቹ የሥራ አካባቢ ለመልካም ውጤት ያበቃል” የሚሉት ፕሬዚዳንቱ ለዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች የሕጻናት ምቹ መዋያ እና ለ200 መምህራን ዘመናዊ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ተካሂዷል ብለዋል። አረንጓዴው ግቢ ለአረንጓዴ ልማት እጁ አይታጠፍምና በተመሠረተበት የአዊ አካባቢ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣ በአረንጓዴ ልማት ሥራ እና በግብርና ላይም በትጋት እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
ከዩኒቨርሲቲው ግቢ በተጨማሪ በቻግኒ አቅራቢያ ስጋዲ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሰፊ የችግኝ ጣቢያ ተቋቁሟል፤ የሀብሃብ፣ ድንች፣ ሩዝ እና ሰንዴ ምርጥ ዘሮችን በማልማት የአርሶ አደሮች ምርት እና ምርታማነት እንዲያድግም ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለአካባቢው ባሕል፣ እሴት፣ ቋንቋ እና ለሀገር በቀል ዕውቀቶች ማደግም የበኩሉን ማኅበራዊ ኀላፊነት እየተወጣ ይገኛል። ለመድኃኒትነት የሚያገለግሉ ሀገር በቀል ዕጽዋት ተጠብቀው የሚያድጉበት ማዕከል በዩኒቨርሲቲው ተዘጋጅቷል።
ዩኒቨርሲቲዎች ከአካባቢያቸው ተነስተው አቅም እና ተደራሽነታቸውን እያሰፉ መጓዝ አለባቸው ያሉት ፕሬዝዳንቱ እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢውን ቋንቋ፣ ባሕል እና እሴት ለማስተዋወቅ የጥናት እና ምርምር ተቋም ገንብቶ እና መዋቅር ዘርግቶ እየሠራ እንደኾነም ገልጸዋል። “የአገው ጥናት ኢኒስቲትዩት” ተቋቁሞ በሥራ ላይ ነው ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ በአገው ባሕል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ሀገር በቀል ዕውቀት እና እሴት ላይ ያተኮሩ ትልልቅ ጥናቶችን ማካሄዱን እና ማሳተሙንም ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው በ2017 ዓ.ም በ48 የቅድመ ምረቃ እና በ28 የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች ሲያስተምራቸው የቆዩ ተማሪዎችን ያስመርቃል። በዚህ 6ኛ ዙር ምርቃት በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በመደበኛ እና በተከታታይ ፕሮግራሞች 3 ሺህ 917፣ በሁለተኛ ዲግሪ 251 እና በተለያዩ ከፍተኛ ዲፕሎማዎች ደግሞ 303 በአጠቃላይ 4 ሺህ 471 ተማሪዎች ይመረቃሉ ብለዋል። ከተማራቂዎች ውስጥ 1 ሺህ 646 ወይም 37 በመቶው ሴት ተማሪዎች መኾናቸውንም ተናግረዋል።
ከሌሎች ዓመታት በተለየ መልኩ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች የሚመረቁበት የዩኒቨርሲቲው 6ኛ ዙር የተማሪዎች የምርቃት መርሐ ግብር ሰኔ 14/2017 ዓ.ም ይካሄዳል። የምርቃት ፕሮግራሙ በአሚኮ የማሰራጫ ጣቢያዎች በቀጥታ ይተላለፋል፤ አድማጭ፣ ተመልካች እና ተከታታዮች የአረንጎዴውን ግቢ ደማቅ ሁነት በአሚኮ በኩል እንዲታደሙም ፕሬዝዳንቱ ጋብዘዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን