
አዲስ አበባ፡ ሰኔ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) እናት ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ የ2025 የባንኮች የሥርዓተ ፆታ አካታችነት ምዘና መስፈርት መሠረት በሴቶች አቀፍ የባንክ አገልግሎት ከሌሎች 30 ባንኮች ተሽሎ በመገኘት ቀዳሚ ባንክ መኾኑ ተገልጿል።
ይህ ዕውቅና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከዓለም ባንክ የሥርዓተ ፆታ ፈጠራ ጋር በመተባበር ባካሄዱት ምዘና የተሰጠ ነው። የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አማካሪ ማርታ ኃይለማርያም እንደገለጹት እናት ባንክ ሴቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርግ አካታች የባንክ አገልግሎት በመዘርጋት እና ሌሎች ሴቶችን በንግዱ ዘርፍ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን በማከናወኑ ከተቀመጠው የአምስት ነጥብ መለኪያ 4 ነጥብ 6 በማምጣት ቀዳሚ ኾኗል።
በሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚኒስትር ድኤታ ማዕረግ የሚኒስትሯ አማካሪ ጌታቸው በዳኔ እናት ባንክ ለሴቶች የተለየ የባንክ አገልግሎት በማቅረብ፣ ለፈጠራ ድጋፍ የሚኾን የባንክ አሠራር በመዘርጋት እና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ያሳየው ውጤት ሀገሪቱ እያካሄደች ላለው የማክሮ ኢኮኖሚ ስኬታማነት እና ለአካታች ፋይናንስ አርዓያ መኾኑን አብራርተዋል።
የእናት ባንክ የቦርድ ሠብሣቢ አስቴር ሰለሞን እንደገለጹት ከባንኩ አመራሮች ከ55 በመቶ በላይ የሚኾኑት ሴቶች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም ከ22 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ሥራ ፈጣሪ ሴቶች 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ያለ ዋስትና በማበደር የራሳቸውን ሥራ እንዲጀምሩ ድጋፍ ተደርጓል።
የብሔራዊ ባንክ እና የዓለም ባንክ የአካታችነት ምዘና መስፈርት የፋይናንስ ተቋማት ሴቶችን እንደ ደንበኛ፣ ሠራተኛ እና አመራርነት ያላቸውን አካታችነት ለመገምገም የሚረዳ ሲኾን በዘርፉ አመራር ላይ ያለውን ልዩነት ለማጥበብም ያግዛል።
የባንኩ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ትዕግስት አባተ እናት ባንክ ሴቶች ላይ ብቻ ትኩረቱን ያደረገ ክፍል በማዋቀር ሴቶችን በቢዝነስ እና መሰል ሥራዎች የማማከር ሥራ መሥራቱ ከተመረጠባቸው መስፈርቶች መካከል አንዱ መኾኑን ተናግረዋል።
የሴቶች የፋይናንስ ማካተት እና ማብቃት ከእናት ባንክ ራዕይ አንዱ ሲኾን ባንኩ በሴቶች መመሥረቱም የዚህ ማሳያ ነው ብለዋል። በዕውቅና እና ምሥጋና ሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዝዳንት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የእናት ባንክ ደንበኞች፣ የቦርድ አባላት፣ ባለአክሲዮኖች፣ ከፍተኛ መሪዎች እና ሠራተኞች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፦ ኢብራሂም መሐመድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን