የዞኑ ተወላጆች አካባቢያቸውን ለማልማት የሚያደርጉት ሁሉን አቀፍ ርብርብ ተስፋ ሰጭ ነው።

8

ሁመራ፦ ሰኔ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት ዓመታት በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በርካታ የልማት ሥራዎች መከናዎናቸውን የዞኑ አሥተዳደር አስታውቋል። ባለፉት ዓመታት በዞኑ በተከናወኑ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ላይ የዞኑ አሥተዳደር ከተለያዩ አካባቢዎች ከተውጣጡ የማኅበረብ ክፍሎች ጋር ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱም ልማትን እና ነፃነትን አጣጥሞ ለመቀጠል ከውጭ እና ከውስጥ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ተቋቁሞ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን የሕዝቡ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መኾኑም ተነስቷል። ለትውልድ ምን ሠርቼ ልለፍ የሚሉ የዞኑ ተወላጆች አካባቢያቸውን ለማልማት የሚያደርጉት ሁሉን አቀፍ ርብርብ ተስፋ ሰጭ መኾኑን የዞኑ ዋና አሥተዳዳሪ እና የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አሸተ ደምለው ገልጸዋል።

የዞኑ ሕዝብ የማንነት እና ወሰን ጥያቄ ከግለሰባዊ የቁስ ፍላጎት በላይ ነው ያሉት አቶ አሸተ ደምለው ማንነታችንን በሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገድ ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራትን እያከናወንን ነው ብለዋል። አቶ አሸተ ደምለው በመንገድ፣ በጤና፣ በትራንስፖርት፣ በግብርና፣ በአገልግሎት እና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ባለሃብቱ፣ ማኅበረሰቡ እና የመንግሥት መዋቅሩ በመቀናጀት እየሠራ መኾኑን አብራርተዋል።

ከልማት ተግባራት ባሻገርም ባሕልን በማሳደግ ሰላምን፣ ፍትሕን እና የዳኝነት ሥርዓትን በአግባቡ በመጠቀም ረገድ የተከናወኑ ተግባራት የነፃነታችን ፍሬዎች መኾናቸው ሊታወቁ ይገባል ነው ያሉት። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ማንነትን ከአማራዊ ማንነት ለመነጠል የሚሞክሩ አካላት ለአማራ እና ለወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ጠላቶች ናቸው ያሉት ደግሞ የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊ ዋኘው ደሳለኝ ናቸው።

አማራዊ ወንድማማችነትን ማጠናከር ነፃነታችንን ለመጎናጸፍ እንዳደረግነው ትግል ሁሉ ማንነታችንን ለማጽናትም ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለዋል። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ አማራዊ የማንነት ጥያቄ ድሮም ኾነ ዘንድሮ ሕጋዊ ነው ያሉት አቶ ዋኘው ይሄንን ፍትሐዊ ጥያቄ በኀሠይል ለመንጠቅ የሚሞክርን ሁሉ መታገል የትውልዱ ግዴታ መኾኑን አንስተዋል።

ከዞኑ እና ከአማራ ክልል ውጭ የሚደረጉ ተገቢ ያልኾኑ እንቅስቃሴዎች አማራዊ ማንነታችንን ለመንጠቅ የሚደረጉ እስከኾኑ ድረስ በጋራ ቆመን እንታገላለን ያሉት ደግሞ የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኀላፊ ልዑል ሀጎስ ናቸው።

የሕወሓት ቡድን በአገዛዝ ዘመኑ በአማራ እና በወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ላይ ያደረሰውን በደል ሁሉም ያውቀዋል ያሉት ኀላፊው በደም ዋጋ የተገኘውን ማንነታችንን በዋጋ እናጸናዋለን ብለዋል። እኛ አማራ ነን እንጂ አማራ እንሁን አላልንም ያሉት ደግሞ የመድረኩ ተሳታፊዎች ናቸው።

ከነፃነት በኋላ የተከናወነውን ልማት ያደነቁት ተሳታፊዎቹ ሰላሙን እና ልማቱን ዘላቂ ለማድረግ ማንነትን ማጽናት ግዴታ መኾኑን ጠቁመዋል። የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ከሥሩ በማስተካከል እና አገልጋይ የመንግሥት ሠራተኛ መፍጠር ተገቢ መኾኑንም ነው ተሳታፊዎቹ ያነሱት።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየጤና ቢሮ ማስፋፊያ እና እድሳት ሰው ተኮር መኾኑን ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ተናገሩ።
Next articleእናት ባንክ በሴቶች አቀፍ የባንክ አገልግሎት በኢትዮጵያ ቀዳሚ ነው።