
ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማእረግ የማኀበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) እና ሌሎች የሥራ ኀላፊዎች የጤና ቢሮን ማስፋፊያ እና እድሳት ጎብኝተዋል።
ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) የቢሮ ማስፋፊያ እና እድሳት ሥራው ዕይታን የሚለውጥ ነው ብለዋል። ሥራው ሙሉ ሕንጻ ማደስ፣ መለወጥ እና መጨመርን ታሳቢ ያደረገ ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ዝግ የነበሩ ቦታዎችን በመክፈት ገጽታን መለወጥ የሚያስችል በመኾኑ አሠራርን ውጤታማ ያደርጋል ነው ያሉት።
ቢሮው እያከናወነ የሚገኘው ግንባታ ክልሉ እየተከተለ ካለው የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ሪፎርም ጋር የሚጣጣም መኾኑንም ተናግረዋል። የቢሮው ዕድሳት እና የማስፋፊያ ሥራ ዲጂታላይዜሽንን ታሳቢ ያደረገ ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ሠራተኞችን እና ተገልጋዮችን ታሳቢ ያደረገ መኾኑንም አንስተዋል።
የግንባታ ማሻሻያ ሥራው ሰው ተኮር መኾኑንም ጠቅሰዋል። ለሁሉም ሠራተኞች የሥራ ከባቢ የሚመች እና የሕጻናት ማቆያንም የያዘ ስለኾነ ከጅምሩ የሚወደስ መኾኑን ገልጸዋል። የቢሮው ዕድሳት እና የማስፋፊያ ግንባታ ሥራ በሠራተኞች ዘንድ የሥራ ቅልጥፍናን፣ ምርታማነትን እና ተነሳሽነትን ይጨምራል ነው ያሉት።
ግንባታው ውበትን ታሳቢ ያደረገ ከመኾኑ ባለፈ የተበታተነ ሥራንም ወደ አንድ ማዕከል ያመጣል ብለዋል። ለሥራው ቅርበት ያላቸውን ኀላፊዎችም በአንድ ላይ የሚያገናኝ መኾኑን ነው የተናገሩት። የግንባታ እና ማስፋፊያ ሥራው የለውጥ ሥራዎችን ያፋጥናል፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ረገድም የሚኖረው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል። መንግሥት እያደረገ የሚገኘውን የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያም ለሕዝብ ያሳያል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ ቢሮው በሁለት ዓይነት መንገድ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። የመጀመሪያው መልሶ የመጠገን እና የማደስ ሥራ ሲኾን ሁለተኛው ማስፋፊያ ነው ብለዋል። እየተከናወነ የሚገኘው ሥራ ምቹ የሥራ አካባቢን ይፈጥራል ያሉት ኀላፊው የአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናንም ያሻሽላል ነው ያሉት።
የእድሳት ሥራው ዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር የተሳሰረ ስለሚኾን የመረጃ አያያዝን ማዘመን በሚያስችል ሁኔታ እየተሠራ ነው ብለዋል። በማስፋፊያ ግንባታው ከ350 በላይ ሰው መያዝ የሚችል ዘመናዊ ትልቅ አዳራሽ አለው ያሉት ኀላፊው ጥልቅ የንጹሕ ውኃ ማግኛ ጉድጓድም ተቆፍሯል። ይህም ዘርፈ ብዙ ግልጋሎት ይሰጣል ነው ያሉት።
የግንባታ እና የማስፋፊያ ሥራው ዓይነተ ብዙ በመኾኑ በቢሮው የሚሰጡ አገልግሎቶችንም ከወረቀት ንክኪ ነጻ ያደርጋል ብለዋል። ለማኅበረሰቡ መረጃ የሚሰጥ ቴክኖሎጂም እንደሚገጥምም አንስተዋል። መሰል የማስፋፊያ እና እድሳት ሥራዎች በዞን እና በወረዳ ደረጃም እንደሚከናወኑም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ሙሉጌታ ሙጬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!