በቡሬ ከተማ የማስፋፊያ ሥራ የተደረገለት የመጀመሪያ እና የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ፡፡

8

ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በበላይነህ ክንዴ ግሩፕ ፊቤላ ኢንዱስሪያል የገንዘብ ድግፍ ማስፋፊያ የተደረገለት የዕድገት በኅብረት የመጀመሪያ እና የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታው ተጠናቅቆ ዛሬ ተመርቋል። ዕድገት በኅብረት የመጀመሪያ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ1971 ዓ.ም ነው የተመሰረተው።

የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር አበበ ዓለማየሁ ትምህርት ቤቱ ከዕድሜው መርዘም አንጻር የመማሪያ ክፍሎቹ አርጅተው ለመማር ማስተማር ሂደቱ እንቅፋት ኾነው መቆየታቸውን በርክክቡ ወቅት ገልጸዋል። ባለሃብቱ በላይነህ ክንዴ የትምህርት ቤቱን ችግር በመረዳት በአጭር ጊዜ እና በፍጥነት በትምህርት ቤቱ አዳዲስ ክፍሎች እንዲገነቡ አድርገዋል።

ባለሃብቱ 15 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ባለ ሁለት ወለል ሕንጻ አስገንብተውም ለአገልግሎት ክፍት ስለማድረጋቸው ነው ያስገነዘቡት። ትምህርት ቤቱ ተሻሽሎ እንዲገነባ መደረጉ አኹን ላይ ተቀብሎ እያስተማራቸው ያሉ ከ1ሺህ በላይ ተማሪዎቸ በምቹ ኹኔታ ለማስተማር እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።

በበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የፌቤላ ኢንዱስሪያል ተወካይ ኀላፊ ዳዊት ገብረስላሴ ፊቤላ ኢንዱስትሪያል በቡሬ ከተማ ሥራ በመጀመሩ የሥራ ዕድል እና የቴክኖሎሎጂ ሽግግር መፍጠሩን ተናግረዋል። ፋብሪካው በቡሬ እና አካባቢው ያሉ ዜጎች የማኅበራዊ ግልጋሎቶች ተጠቃሚ ማድረግ ስለመቻሉም አብራርተዋል።

አቶ ዳዊት ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ ፊቤላ ኢንዱሰትሪያል የቡሬ እና አካባቢው ማኅበረሰብን ተጠቃሚ ለማድረግ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ወጭ ስለማድረጉም ነው የገለጹት፡፡ አቶ ዳዊት የዕድገት በኅብረት የመጀመሪያ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ለመጠገን 30 ሚሊዮን ብር ወጭ ማድረጉንም ተናግረዋል።

ለተገነቡ ሁሉም ክፍሎች ደረጃውን የጠበቀ ወንበር እና ጠረንጴዛ በማሟላት ለሥራ ዝግጁ ተደርጓል ብለዋል፡፡ የቡሬ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደሳለው ፍቃዱ በበኩላቸው ፊቤላ ኢንዱስትሪያል በቡሬ እና አካባቢው የኢንዱስትሪ የሥራ ባሕል እንዲስፋፋ እና ለበርካቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ማድረጉን ጠቁመዋል።

ድርጅቱ በተግባር የሚታዩ ማኅበራዊ ኅላፊነቶችን በመወጣት ረገድ በአርዓያነት የሚጠቀስ ሥራ እያከናወነ በመኾኑ ለድርጂቱ እና ለባለቤቱ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ በላይነህ ክንዴ ግሩፕ በፋውንዴሽኑ አማካኝነት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ባለፉት አራት ዓመታት ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ ለማኅበራዊ ኀላፊነት ወጭ ያደረገ ሲኾን ለባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም ቀሪ ሥራዎች ማጠናቀቂያ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ከምዕራብ ጎጃም ዞን ኮምንኬሽን መምርያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሥልጠናው ሴት መሪዎች በቀውስ ጊዜ ተጠልፈው የሚወድቁ ሳይኾኑ ችግሮችን ተቋቁመው መሥራት እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው።
Next articleየጤና ቢሮ ማስፋፊያ እና እድሳት ሰው ተኮር መኾኑን ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) ተናገሩ።