ሥልጠናው ሴት መሪዎች በቀውስ ጊዜ ተጠልፈው የሚወድቁ ሳይኾኑ ችግሮችን ተቋቁመው መሥራት እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው።

9

ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ለሚገኙ ሴት መሪዎች በባሕር ዳር ከተማ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የቀውስ ጊዜ አመራር እና ከቀውስ ማገገሚያ ዙሪያ ሥልጠና ተሰጥቷል። በሥልጠናው የተሳተፉት መሪዎች ሥልጠናው የሥራ መነቃቃት እና ተነሳሽነት እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

ከአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር የመጡት ወይዘሮ አምባነሽ ስሜነህ ሥልጠናው ሴት መሪዎች ያለባቸውን ድርብ ኀላፊነት በቀውስ ጊዜ እንዴት መወጣት እንዳለባቸው አቅም እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ የተከሰተው ቀውስ በሥራቸው ላይ የፈጠረውን ጫና ተቋቁመው እንዲሠሩ የሚያስችል እና የነበረውን መፋዘዝ የሰበረ መኾኑንም ገልጸዋል።

ከደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር የመጡት ወይዘሮ ፈንታየ አለነ በበኩላቸው ሥልጠናው ለቀጣይ ሥራዎች ስንቅ የሚኾን እና ለሥራቸው አጋዥ መኾኑን ጠቅሰዋል። አሁን ባለው የቀውስ ጊዜ ሴቶችን እንዴት ማገዝ እንደሚገባ ራሳቸውን እንዲፈትሹ እንዳደረጋቸውም ተናግረዋል።

ሥልጠናው ለሚሠሯቸው ሥራዎችም መንገድ ጠራጊ እንደኾነ ገልጸዋል። በተጨማሪም ሥልጠና ላላገኙ ሌሎች ሴት መሪዎች ያገኙትን ዕውቀት ለማጋራት ዝግጁ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

የሥልጠናው አካል በኾነው ጉብኝት በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በግላቸው እና በማኅበር ተደራጅተው በተለያዩ ሥራዎች የተሰማሩ ውጤታማ ሴቶችን ተሞክሮ ማየታቸውን ገልጸዋል። ሥራዎቹን ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመውሰድ በተግባር ሊለወጥ የሚችሉ መኾናቸውን መመልከታቸውንም ተናግረዋል።

ጠባብ ቦታ ላይ የዶሮ እርባታ ሥራ፣ ሐይቅ እና ወንዝ በሌለበት አካባቢ ሰው ሠራሽ ኩሬዎችን በመጠቀም የዓሳ ምርት ማምረት እንደሚቻል ከጉብኝቱ መረዳታቸውን አንስተዋል።የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ በዚህ ዓመት የተለያዩ ሥልጠናዎች በተለያዩ ጊዜያት መሰጠታቸውን ገልጸዋል።

ሥልጠናው ሴት መሪዎች በቀውስ ጊዜ ችግር ሲፈጠር ተጠልፈው የሚወድቁ ሳይኾኑ ችግሮችን ተቋቁመው መሥራት የሚችሉ መኾናቸውን እንዲያሳዩ ከሚደረጉ ጥረቶች አንዱ መኾኑን አመልክተዋል። ሴቶች አስፈላጊው ትኩረት ከተሰጣቸው እና ከታገዙ በሥራዎቻቸው ውጤታማ ሊኾኑ እንደሚችሉም ገልጸዋል። ለአማራ ክልል ሴት መሪዎች የቀውስ ማገገሚያ እና የቀውስ ጊዜ አመራር ዙሪያ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የነበረው ሥልጠና ዛሬ ተጠናቅቋል።

ዘጋቢ፡ ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleየተቀዛቀዘውን ምጣኔ ሀብት ማነቃቃትን ያለመ የንግድ ትርዒት እና ባዛር በደብረ ታቦር ከተማ ተጀምሯል።
Next articleበቡሬ ከተማ የማስፋፊያ ሥራ የተደረገለት የመጀመሪያ እና የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ፡፡