በ115 ሚሊዮን ብር ሊገዛ የነበረው ፋብሪካ 315 ሚሊዮን ብር ውል ተይዞበታል፤ የፋይናንስ ችግርም ገጥሞታል፡፡

313

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 21/2012 ዓ.ም (አብመድ) የባሕር ዳር ጨርቃ ጨርቅ አክሲዮን ማኅበር በፋይናንስ ችግር ምክንያት የኅልውና አደጋ እንደገጠመው አስታወቀ፡፡

በ1954 ዓ.ም በጣሊያን መንግሥት የ9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጭ እንደተገነባ ይነገርለታል፤ የቀድሞው የባሕር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ እና የአሁኑ ባሕር ዳር ጨርቃ ጨርቅ አክሲዮን ማኀበር፡፡ የባሕር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በንጉሠ ነገሥቱ እና በደርግ ዘመነ መንግሥታት በመንግሥት ስር ይተዳደር ነበር፡፡ በዘመነ ኢሕአዴግ ደግሞ ወደ መንግሥት የልማት ድርጅት ተዛውሮ እስከ 2009 ዓ.ም ድረስ ቆይቷል፡፡

በ2009 ዓ.ም የፌዴራሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ለጥረት ኮርፖሬት በ115 ሚሊዮን ብር ለመሸጥ ስምምነት ላይ ደረሰ፡፡ ነገር ግን የውል ስምምነቱ በግልፅ ባልታወቀ መልኩ በውል ወቅት 200 ሚሊዮን ብር ተጨምሮበት በ315 ሚሊዮን ብር ገዥ እና ሻጭ ተዋዋሉ፡፡ የአጠቃላዩን ዋጋ 35 በመቶ አምባሰል የንግድ ሥራዎች ድርጅት ክፍያ ፈፀመ፡፡

“ውሉ ከዚህ ያለፈ ውስብስብ እና ግልፅ ያልነበሩ ችግሮች ነበሩበት” ያሉት የባሕር ዳር ጨርቃ ጨርቅ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አበበ ባየ (ዶክተር) ናቸው፡፡ “ከዚህ በተጨማሪም በውሉ ‘ፋብሪካው ያልታወቀ እና የታወቀ ዕዳ ቢኖርበት ገዥ ይከፍላል’ የሚል ሐሳብ በመካተቱ ከውል በኋላ የመጣ እና ያልታወቀ 112 ሚሊዮን ብር ከፍሏል” ብለዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በውል ስምምነቱ ዕዳውን ከፍሎ የስመ ንብረት ዝውውር እስኪያደርግ ድረስ ከባንክ መበደር እንዳይችል መደረጉን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡
ዛሬ ላይ 1 ሺህ 354 ሠራተኞችን በውስጡ ያቀፈው እና ከባሕር ዳር ከተማ መቆርቆር ጋር የተሳሰረ ስምና ዝና ያለው አክስዮን ማኅበሩ ግልፅ ባለቤት አጥቶ ኅልውና አደጋ ውስጥ መግባቱ ታውቋል፡፡

በክልሉ ርእሰ መሥተዳድር ተመሥገን ጥሩነህ የተመራ የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት ፋብሪካውን ዛሬ ጎብኝተዋል፡፡ ከፋብሪካው ሠራተኞች እና ኃላፊዎች ጋር ቆይታ ያደረጉት ርእሰ መሥተዳድሩ “ባሕር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ለክልሉ መንግሥት ካለው ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳ ባሻገር ከባሕር ዳር ከተማ ምሥረታ ጋር የተሳሰረ የዘመናት ታሪክ ያለው በመሆኑ ለተፈጠረው ወቅታዊ ችግር መፍትሔ ለማፈላለግ እንሠራለን” ብለዋል፡፡ በተለይም ለፋብሪካው የባለቤትነት ጉዳይ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ርእሰ መሥተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡

አብመድ በባሕር ዳር ጨርቃ ጨርቅ አክሲዮን ማኅበር ዚሪያ ያለውን መሠረታዊ ችግር በቀጣይ የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግሮ ምላሻቸውን ይዞ ይቀርባል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
ዩቱዩብ https://bit.ly/38mpvDC ያገኛሉ፡፡

Previous articleበ24 ሰዓታት ውስጥ በ137 ሰዎች ላይ የኮሮና ቫይረስ ተገኝቷል፡፡
Next articleአስተማሪ ተማሪዎች በበረኸት፡፡