የተቀዛቀዘውን ምጣኔ ሀብት ማነቃቃትን ያለመ የንግድ ትርዒት እና ባዛር በደብረ ታቦር ከተማ ተጀምሯል።

13

ደብረ ታቦር: ሰኔ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን፣ የደብረ ታቦር ከተማ አፈጉባኤ ቄስ መልካሙ ላቀው እና የከተማ አሥተዳደሩ የመምሪያ ኀላፊዎችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ብንያም ባዬ በተከሰተው ግጭት ምጣኔ ሀብቱ ተቀዛቅዞ መቆየቱን ተናግረዋል። የንግድ ትርዒት እና ባዛሩ ዋና ዓላማም በከተማዋ የተገኘውን ሰላም በመጠቀም ተዳክሞ የነበረውን ንግድ ለማነቃቃት እንደኾነ ገልጸዋል። ሸማቾች እና ነጋዴዎችን በማቀራረብ ጥራት ያላቸውን ምርቶች በተመጣጠነ ዋጋ በማቅረብ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም አንስተዋል።

ለአሥር ተከታታይ ቀናት በሚቆየው የንግድ ትርዒት እና ባዛር የአካባቢው ማኅበረሰብ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል። የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን ከተማዋ ከአንፃራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም እየመጣች መኾኑን አንስተዋል። የተገኘውን ሰላም በመጠቀም ባዛሩ መዘጋጀቱን ነው የተናገሩት።

በሰላም እጦቱ የምርት አቅርቦት ችግር አጋጥሞ ነበር ያሉት ከንቲባው በአሁኑ ወቅት ግን አንጻራዊ ሰላም በመምጣቱ ችግሩ እየተፈታ መኾኑን አንስተዋል። ማኅበረሰቡ በተዘጋጀው ባዛር ከነጋዴዎች ጋር የሚፈልገውን ምርት የሚያገኝበት፣ ነጋዴዎችም ያመጡትን ምርት የሚያስተዋውቁበት እና የተሻለ ግብይት የሚያደርጉበት እንደሚኾንም ተናግረዋል። ተሳታፊ ነጋዴዎችም ከንግዱ ባለፈ የከተማዋን ታሪካዊ ቦታዎች በመጎብኘት ባሕልን ማስተዋወቅ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በየዘመኑ የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ሴቶች የማይተካ ሚና አላቸው” ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር)
Next articleሥልጠናው ሴት መሪዎች በቀውስ ጊዜ ተጠልፈው የሚወድቁ ሳይኾኑ ችግሮችን ተቋቁመው መሥራት እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው።