“በየዘመኑ የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ሴቶች የማይተካ ሚና አላቸው” ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር)

15

ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ሴት የሰላም አምባሳደሮችን ማደራጀት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ” በሚል መሪ መልዕክት በተለያዩ አደረጃጀቶች እየተሳተፉ ለሚገኙ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ሥልጠና በባሕር ዳር ከተማ እየተሰጠ ነው።

በአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) በየዘመኑ የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ሴቶች የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል። ሴቶች ለመረጃ ቅርብ ናቸው፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ሰፋ ያለ ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ አላቸው ስለኾነም የሴቶችን አቅም ማጎልበት ለሰላም መስፈን የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው አንስተዋል።

ግጭት ባለበት አካባቢ መፍትሄ ለማምጣት ሴቶች ሰፊ ሚና አላቸው ነው ያሉት። እያጋጠመን ያለውን ግጭት በአግባቡ ለመፍታት ሴቶች ተሳትፏቸውን በማላቅ በቤተሰብ ደረጃ ግጭት እንዳይፈጠር ማድረግ እንደሚገባቸውም ነው ያስገነዘቡት።

የሚያጋጩንን ትርክቶች ጥሎ አንድ የሚያደርጉንን ትርክቶች መገንባት፣ መሠባሠብ፣ አንድ መኾንን እና የውስጥ ሰላምን መፍጠር የግድ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ሴቶች ብልኾች ስለኾናችኹ ሰላም ከቤታችሁ እንዲጀምር ኹሉንም አሸናፊ የሚያደርገውን መስመር እንድትከተሉ በየአደረጃጀቶቻችሁ ያለመታከት መሥራት ይጠበቅባችኋል ሲሉም አሳስበዋል።

በሥልጠናው የተገኙት በኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስቴር የግጭት አሥተዳደር መሪ ሥራ አሥፈጻሚ ይርጋ መንግሥቱ ሴቶች የሚፈጠሩ ችግሮችን አስቀድሞ ለመከላከል እና ለመፍታት ሚናቸው ከፍ ያለ እንደኾነ ገልጸዋል። ሰላም ለሁሉም ይጠቅማል፣ ከሰላም ሁሉም ያተርፋል ነው ያሉት። ሰላም የሚጀምረው ከግለሰብ ነው፣ ከዚያም ወደ ማኅበረሰብ እና ወደ ሀገር ያድጋል ብለዋል።

የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ አኹን የተፈጠረው ቀውስ አካል እንዳይኾን ተሠባሥቦ መነጋገር እና መምከር እንደሚገባም ተናግረዋል። ካለው ችግር ለመውጣት ሴቶች በየአካባቢው ባሉት አደረጃጀቶች መሠረት መነጋገር እና በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።

የሰላም ሚኒስቴር ግጭት በተፈጠረባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ እየኾነ ግጭቶች በዘላቂነት እንዲፈቱ ልዩ ልዩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም እየሠራ መኾኑንም አመላክተዋል። በአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሴቶች ክንፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኢሌኒ ዓባይ የተዘጋጀው ሥልጠና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ስለሰላም፣ ስለግጭት እና ደኅንነት የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል ያለመ መኾኑን ገልጸዋል።

ሠልጣኞች በየአካባቢያቸው ሲመለሱ የሰላም አምባሳደር ኾነው እንደ ክልል ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ርብርብ አወንታዊ ሚና መጫወት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል። ሴቶች ለሰላም ቅርብ ናቸው፣ በየትኛውም ደረጃ ሰላም ሲደፈርስ ሰላምን ለመመለስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው ነው ያሉት።

ኀላፊዋ በሀገሪቱ በተፈጠሩት ቀውሶች ሴቶች የግጭቱ ጠንሳሾች ሳይኾኑ ግንባር ቀደም ተጎጅዎች እና የችግሩ ገፈት ቀማሾች መኾናቸውንም አመላክተዋል። አሁን ላይ ከክልል እስከ መንደር የደረሱ በርካታ ውይይቶች ስለማድረጋቸውም አብራርተዋል።

የሰላም አምባሳደር የኾናችሁ የሥልጠናው ተሳታፊ ሴቶች የእናት ሀገር ኢትዮጵያ እና የአማራ ሕዝብ አደራ እንዳለባችኹ ተገንዝባችኹ ሁሉም ችግሮች በምክክር እንዲፈቱ ሚናችሁን እንድትወጡ ሲሉ አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous article‎‎የርዕዮት ዓለም ልዩነት ቢኖርም የምትገነባው የጋራ ሀገር መኾኗን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ተናገሩ።
Next articleየተቀዛቀዘውን ምጣኔ ሀብት ማነቃቃትን ያለመ የንግድ ትርዒት እና ባዛር በደብረ ታቦር ከተማ ተጀምሯል።