‎‎የርዕዮት ዓለም ልዩነት ቢኖርም የምትገነባው የጋራ ሀገር መኾኗን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ተናገሩ።

12

ጎንደር: ሰኔ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የተወጣጡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እና አባላት በጎንደር ከተማ የተሠሩ እና እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ያገኘናቸዉ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈጻሚ አባል ማሩ ጃኔ ጎንደር ከተማ ሕብረ ብሔራዊ ከተማ ናት ብለዋል። ከተማዋ ወደ ቀደመ ገናና ታሪኳ እንድትመለስ እየተሠራ ያለው ተግባር የሚበረታታ እንደኾነ አንስተዋል።

‎የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲ የጋራ ምክር ቤት የሴቶች ክንፍ ሰብሳቢ እና የኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ፓርቲ መስራች እና ሥራ አስፈጻሚ እጸገነት ተስፋዬ የጎንደር ከተማ የውኃ ችግርን ለመቅረፍ ታቅዶ እየተሠራ ያለውን የመገጭ መስኖ ፕሮጀክት መጎብኘታቸውን ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ በመልካም ቁመና ላይ ኾኖ መመልከታቸውንም አንስተዋል። የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የሚበረታቱ ናቸው ነው ያሉት።

‎ጎንደር ከተማን ሲመለከቱ ለመጀመሪያ ጊዜ መኾኑን የነገሩን ደግሞ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የሴቶች ክንፍ ምክትል ሰብሳቢ እና የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ገሊላ ኀይሉ ናቸው። የጎንደር ከተማ ሕዝብ እንግዳ ተቀባይ መኾኑንም በጉብኝታቸዉ መታዘባቸውን ተናግረዋል። በከተማው እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች የሚደነቁ መኾናቸውንም አስረድተዋል።

‎የርዕዮት ዓለም ልዩነት ቢኖርም የምትገነባው የጋራ ሀገር ናት ያሉት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ለሀገር ሰላም ግንባታ በጋራ የመሥራት ልምድን ባሕል ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። ሀገር የሰላም እጦት ሲገጥማት ልዩነትን ከማስፋት ይልቅ በጋራ ቁጭ ብሎ ችግርን መፍታት ያስፈልጋል ነው ያሉት። በቀጣይም ለዘላቂ ሰላም በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ መኾናቸውን ተናግረዋል።

‎የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች እና አባላት በከተማው ባዩት የልማት ሥራ ደስተኛ መኾናቸውን እንደገለጹላቸው ተናግራዋል። ጎንደር የሁሉም ከተማ ናት ያሉት አቶ ቻላቸው የፋሲል አብያተ መንግሥታት የኢትዮጵያውያን እና የዓለም ሀብት ነው ብለዋል።

‎ፓርቲያቸው ብልጽግና በጋራ መሥራትን መርሕ አድርጎ እየሠራ መኾኑንም አንስተዋል። በከተማው የተጀመረውን ሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማት በጥራት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- አዲስ ዓለማየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በምዝገባ ያጣናውን በውጤት ለመካስ ትብብር እየተደረገ ነው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)
Next article“በየዘመኑ የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ሴቶች የማይተካ ሚና አላቸው” ዘሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር)