“በምዝገባ ያጣናውን በውጤት ለመካስ ትብብር እየተደረገ ነው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)

15

ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ቅድመ ዝግጅትን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም የ6ኛ እና የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተናዎችን በሰላም ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል። ፈተናዎቹ በሰላም እንዲጠናቀቁ ሁሉም ትብብር አድርጓል ያሉት ኀላፊዋ በተለይም ማኅበረሰቡ ከፍተኛ ትብብር ማድረጉንም ገልጸዋል።

ማኅበረሰቡ ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት ወስዶ፣ ትምህርት ቤቶችን ጠብቆ ፈተናዎች በሰላም እንዲጠናቀቁ አድርጓል ነው ያሉት። ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

የ12ኛ ክፍል ፈተና ከሰኔ 23/2017 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚሰጥ የተናገሩት ቢሮ ኀላፊዋ ፈተናው በወረቀት እና በኦንላይን እንደሚሰጥም ገልጸዋል። በክልሉ 99 ሺህ 800 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ፈተናዎችን ይፈተናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል። 4 ሺህ የሚኾኑት ተማሪዎች በሁለተኛው ዙር እንደሚፈተኑም አንስተዋል። ሁለተኛው ዙር በነሐሴ 2017 ዓ.ም መጨረሻ ላይ እንደሚሰጥም ገልጸዋል። የትምህርት ሚኒስቴር የሁለተኛ ዙር ፈተና እንዲዘጋጅ ስላደረገ ምስጋና ይገባዋል ነው ያሉት።

22 ሺህ 400 የሚኾኑት ተማሪዎች በኦንላይ እንደሚፈተኑም ገልጸዋል። ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር ቴክኖሎጂን የተላመደ ትውልድ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ተማሪዎች የቴክኖሎጂ ልምምድ እንዲያደርጉ ላደረጉ ዩኒቨርሲቲዎች እና ኮሌጆችም ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል። ሁሉም ቁጭት እና እልህ ስላለበት በምዝገባ ያጣናውን በውጤት መካስ አለብን በሚል ትብብር እያደረገ ነው ብለዋል።

የተመዘገቡት ተማሪዎች ከሚጠበቀው አንጻር ጥቂት ቢኾኑም የተሻለ ውጤት ለማምጣት እየተሠራ ነው ብለዋል። ትምህርት የትብብር ሥራ ነው ያሉት ኀላፊዋ ልጆቻችንን ለማብቃት ሁሉም የራሱን ድርሻ መወጣት አለብን ነው ያሉት። የትምህርት ተቋማትም የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንዲወጡም አሳስበዋል። ቀድሞ ያወቀ ማኅበረሰብ አሁን ላይ ወደ ኋላ መመለስ እንደማይገባውም ገልጸዋል። ጥራት ላይ መሥራት በሚገባን ጊዜ የተሳትፎ ጉዳይ ላይም ጥያቄ የሚነሳበት ኾኗል ነው ያሉት። ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ ማኅበረሰቡ እና የጸጥታ ተቋማት የድርሻቸውን መወጣት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

የልጆቻችን ትምህርት አይቋረጥም ብለው ያስተማሩ ወላጆች አሉ ያሉት ኀላፊዋ ድካማቸው ፍሬ እንዲያፈራ ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ ማድረግ ይገባቸዋል ነው ያሉት። ተማሪዎች የሥነ ልቦና ጫና ሳይደርስባቸው እንዲፈተኑ እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸውም ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች በብዙ ችግር ውስጥ ኾነው የሚመጡ ተማሪዎችን ተንከባክበው እንዲያስፈትኑም አሳስበዋል። የተማሪዎችን ደኅንነት በጠበቀ መልኩ እንዲፈተኑ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የ25 ዓመታቱ ዕቅድ ከችግር ላይ ትምህርት የወሰደ የቁጭት ዕቅድ ነው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)
Next article‎‎የርዕዮት ዓለም ልዩነት ቢኖርም የምትገነባው የጋራ ሀገር መኾኗን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ተናገሩ።