“የ25 ዓመታቱ ዕቅድ ከችግር ላይ ትምህርት የወሰደ የቁጭት ዕቅድ ነው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)

16

ባሕር ዳር: ሰኔ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) የ25 ዓመታትን አሻጋሪ እና ዘላቂ ልማት ዕቅድን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም የአማራ ክልል በሁለት ዋና ዋና አዙሪት ውስጥ ውሎ ማደሩን ገልጸዋል። አንደኛው የግጭት አዙሪት ነው። ችግሮቻችን በምክክር እና በውይይት የሚፈቱ ኾነው ሳለ ወደ ግጭት አምርተው ሃብት ጠፍቷል፣ ውድመት አስከትሏል ነው ያሉት። ሌላኛው አዙሪት ደግሞ ድህነት ነው ብለዋል።

ከገጠሙ ችግሮች ለመውጣት ደግሞ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚፈጸም እና አሻጋሪ ዕቅድ ያስፈልጋል ያሉት ኀላፊዋ ከችግሮች ለመውጣትም አሻጋሪ እና ዘላቂ የልማት ዕቅድ መታቀዱን ገልጸዋል። ዕቅዱ በትውልዱ ላይ ቁጭትን በመፍጠር፣ የትውልድ ልዕልናን የሚያንጽ ነው ብለዋል።

ከሌሎች ዕቅዶች የሚለየው ትውልድ ላይ ቁጭትን እና እልህን የሚፈጥር መኾኑን ገልጸዋል። በትውልዱ ላይ ቁጭት መፍጠር ካልቻልን ከችግሩ በዘላቂነት መውጣት አንችልም ነው ያሉት። ትውልድን የሚያሻግር ዕቅድ ማቀድ አስፈላጊ መኾኑንም ተናግረዋል።

“የ25 ዓመታቱ ዕቅድ በእልህ ላይ የተመሠረተ፣ ከችግር ላይ ትምህርት የወሰደ፣ የቁጭት ዕቅድ ነው” ብለዋል። ከችግር ላይ መፍትሔ በመውለድ መፍታት ካልተቻለ ሁልጊዜ ስለ ችግር እና ግጭት እያወሩ መቀጠል ከችግር እንደማያወጣም አስታውቀዋል።

የ25 ዓመቱ ዕቅድ ከቀደሙት ዕቅዶች የተለየ አተያይ እና የመዳረሻ ግብ ያለው መኾኑንም አንስተዋል። ከ25 ዓመታት በኋላ የአማራ ክልል አቅም ያለው እና ሁለንተናዊ ብልጽግና የተረጋገጠበት ክልል እንዲኾን ማድረግ ነው ብለዋል። ክልሉ በቴክኖሎጂ፣ በምጣኔ ሃብት፣ በሰብዓዊ ልማት የበለጸገ የማድረግ ራዕይ የያዘ መኾኑን አንስተዋል።

ዕቅዱን ስኬታማ ለማድረግ ደግሞ ወጣቶች ሳይንሳዊ የኾነ ዕውቀት እንዲኖራቸው፣ በቴክኖሎጂ የተካኑ እና ዓለማቀፋዊ ተወዳዳሪ እንዲኾኑ ማድረግ ግድ ነው ብለዋል። የመጀመሪያው የአምስት ዓመት ዕቅድ ደግሞ እንደማስፈንጠሪያነት የሚወሰድ መኾኑን አንስተዋል።

ቀዳሚው ተግባር የክልሉን ሰላም እና ደኅንነት እና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ መኾኑን ገልጸዋል። የክልሉን ሕዝብ ባሕሎች፣ እሴቶች እና ወጎችን ማዳበር፣ በሥነ ምግባሩ የታነጸ ትውልድ ማፍራት ተከታዩ ተግባር ነው ብለዋል። የተዛነፉ የሥነ ምግባሮችን፣ እሴቶችን እና ባሕሎችን ማስተካከል እንደሚገባም አንስተዋል። በባሕል እና በታሪክ ላይ ጎላ ያለ ሥራ መሥራት አንዱ ስትራቴጂ ግብ መኾኑን ነው የተናገሩት።

ጥራት እና ብቃት ያለው ምጣኔ ሃብት መገንባታም ሌላው ጉዳይ ነው ብለዋል። በዚህ ዘመን ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ማድረግ የሚቻለው በትምህርት ነው ያሉት ኀላፊዋ ትምህርት ላይ ትኩረት መስጠት ይገባል ነው ያሉት። ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ያለው እና ዘመኑን የዋጀ ዕውቀት ያለው ትውልድ ለመፍጠር የሚያስችል ዕቅድ መታቀዱንም ገልጸዋል።

ትምህርት ላይ በብዙ እጥፍ በመሻገር ያለፈውን ጎደሎ መሙላት፣ በቀጣይም ተወዳዳሪ መኾን ያስፈልጋል ነው ያሉት። ትምህርት የምጣኔ ሃብት እና የሥልጣን ተስተካካይነት ማረጋገጫ ነው ያሉት ኀላፊዋ በትምህርት ላይ የገጠመን ችግር አሻግረን እንድናስብ የሚያደርግ ነው ብለዋል። በትምህርት ዘርፉ ያለውን የተሳትፎ እና የጥራት ችግር የሚፈታ ዕቅድ መታቀዱንም ገልጸዋል።

ትውልዱ ትምህርት እንዳይማር የሚከለከልበት፣ የተሠሩ ትምህርት ቤቶች እንዲፈርሱ የሚደረግበት እና ወደኋላ የሚመልስ ችግር እንደገጠመ ነው ያነሱት። ዕቅዱም የገጠመውን ችግር ታሳቢ በማድረግ መፍትሔ የሚያመላክት መኾኑን ነው የተናገሩት።

እንደ ሀገር ያለውን ሀብት ወደ ላቀ ደረጃ መጠቀም ሲገባ ያለውን ማውደም እና ማጥፋት እንደማይገባም ገልጸዋል። የቅድመ መደበኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ ላይ ትኩረት እንደሚሰጥባቸውም ተናግረዋል። በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የነበረውን ችግር የሚፈትሽ ዕቅድ መኾኑንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምራ ትምህርትን የተለማመደች፣ የራሷን ፊደል የቀረጸች ናት ያሉት ኀላፊዋ ከጥንት ጀምሮ ለትምህርት ትኩረት በሰጠች ሀገር ውስጥ ተሳትፎን ማረጋገጥ ለምን አልተቻለም? የሚለው ሊመለስ የሚገባው ጉዳይ ነው ብለዋል። ዝቅተኛ የትምህርት ሽፋን አለ የሚሉት ኀላፊዋ በሌላ በኩል ደግሞ ከፍተኛ የሥራ አጥነት ችግር አለ፣ ይህ የሚጣረስ ጉዳይ መልክ መያዝ አለበት ነው ያሉት። እንደ ክልል ከፍተኛ ቁጥር ያለው አገልጋይ አለ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የአገልግሎት ችግር አለ፣ የመልካም አሥተዳደር ችግር ሕዝቡን ይንጠዋል። ለምን? የሚለው መመለስ አለበት ብለዋል።

እንደ ሀገር የሚኖረውን የኀይል ተሳትፎ መፈተሽ እንደሚገባም ገልጸዋል። የትምህርት ሥርዓቱን ከፖለቲካ እና ምጣኔ ሃብት እይታ አንጻር የፈተሸ ዕቅድ መኾኑንም አመላክተዋል። በትምህርት ላይ ያለው መስተጋብር ችግርን የሚፈታ ዕቅድ እንደኾነም ገልጸዋል። ለሁሉም መሠረቱ ትምህርት ነው በሚል እይታ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የጋራ ጥምረት ፈጥረው እንዲሠሩ የሚያደርግ ዕቅድ ነው ብለዋል።

በጤናው ዘርፍም የታቀደው ዕቅድ የዕይታ ለውጥ እንዳለው ነው የተናገሩት። የልማት ግቡ ደስተኛ እና ጤነኛ ማኅበረሰብ መፍጠር ነው ያሉት ኀላፊዋ ዕድገት እና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ጤናማ ማኅበረሰብ መፍጠር ግድ ይላል ብለዋል። በጥልቀት በማየት የታቀደ ዕቅድ መኾኑን ነው የገለጹት። ሁሉም የሚነሳው የተማረ እና ጤነኛ ማኅበረሰብ ሲፈጠር መኾኑን ገልጸዋል። ጤነኛ ማኅበረሰብ ማለት በአስተሳሰቡ፣ በአረዳዱ እና በሌሎች ጉዳዮች የተሻለ ግንዛቤ ያለው እንደማለት ነው ብለዋል።

የአካል ጉዳተኞች፣ የአረጋውያን፣ የሴቶች እና የሕጻናት አካታችነትን እና ፍትሐዊነትን ባገናዘበ መልኩ የታቀደ ዕቅድ መኾኑንም ተናግረዋል። “ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ማካተት እና ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ ትልቁ የልማት ግባችን ነው” ብለዋል። ዘላቂ ሰላምን እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ሊካተት እና ፍትሐዊነት ሊረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት።

የጤና ማኅበረሰብ ለመፍጠር፣ የሀገር ፍቅርን ለማዳበር እና ሀገር ወዳድ ትውልድ እንዲገነባ አካታችነት እና ፍትሐዊነት ወሳኝ መኾኑንም ተናግረዋል። ማኅበራዊ ውቅርን ለማጠንከር የሃይማኖት ተቋማት ላይ ባሕሎች እና እሴቶች ላይ መሥራት ይገባል ብለዋል።

አሻጋሪ ዕቅዱን ውጤታማ ለማድረግ የመጀመሪያውን ድርሻ የሚወስዱት መንግሥት እና የመንግሥት አካላት ናቸው ያሉት ኀላፊዋ በዕቅዱ ላይ በርካታ ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባውም ተናግረዋል። ያለ ማኅበረሰብ ተሳትፎ ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደማይቻልም አንስተዋል። መተባበርን፣ መደማመጥን እና የጋራ አቋም መያዝ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። ከሌሎች ጋር የሚኖረውን መስተጋብር መረዳትም ለዕቅዱ መሳካት ወሳኝ ጉዳይ መኾኑንም አመላክተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ፈተናዎችን በፍጥነት ለመቅረፍ ትኩረት ያደረገ ጉባኤ ሊካሄድ ነው።
Next article“በምዝገባ ያጣናውን በውጤት ለመካስ ትብብር እየተደረገ ነው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)