ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ፈተናዎችን በፍጥነት ለመቅረፍ ትኩረት ያደረገ ጉባኤ ሊካሄድ ነው።

12

አዲስ አበባ፡ ሰኔ 12/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአፍሪካ ኅብረት አባል ሀገራት እና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ቀጣናዊ ፎረም በመንግሥት አገልግሎት አሥተዳደር ዙሪያ 10ኛ ዙር ኮንፈረንስ ይካሄዳል። ጉባኤው በአዲስ አበባ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ለሦስት ቀናት እንደሚካሄድ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በመግለጫው አስታውቋል።

መግለጫውን የሰጡት የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሉ (ዶ.ር) በኮንፈረንሱ የመንግሥት ተቋማት ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን እንዲቋቋሙ እና ለብዙ ጊዜ የተከማቹ ከአገልግሎት ጋር የተያያዙ ፈተናዎችን በፍጥነት በመቅረፍ ዙሪያ ትኩረት ተደርጎ ውይይት ይካሄድበታል ብለዋል።

በሁለተኛ የሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ቀጣናዊ ፎረም ታዳጊ ሀገራት በተባበሩት መንግሥታት እና በአፍሪካ ኅብረት የተቀመጡ ግቦችን ለመፈፀም እና ለማስፈጸም ያለባቸውን የአቅም ክፍተት ለመሙላት የሚያስችሉ ውይይቶች የሚካሄድበት ፎረም መኾኑን ተናግረዋል።

በኮንፈረንሱ ኢትዮጽያ የተጀመረውን የመንግሥት አገልግሎት እና አሥተዳደር በኤግዚቢሽን ለተሳታፊዎች ለዕይታ እንደምታቀርብም ገልጸዋል። ኮንፈረንሱ በየሁለት ዓመቱ የሚከናወን ሲኾን 9ኛው ዙር ኮንፈረንስ በዚምባቡዬ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

ዘጋቢ፦ ራሔል ደምሰው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

Previous articleሴቶች ለሰላም ግንባታ ስለሚኖራቸው ሚና ያተኮረ ሥልጠና በባሕር ዳር ከተማ እየተሰጠ ነው።
Next article“የ25 ዓመታቱ ዕቅድ ከችግር ላይ ትምህርት የወሰደ የቁጭት ዕቅድ ነው” ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር)